የአሠልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ መድን 1-3 ድሬዳዋ ከተማ

“ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ታግለናል ፤ የድካማችንን ዋጋም አግኝተናል” ዮርዳዮስ ዓባይ

“ከጨዋታው አቻ ይገባን ነበር” ገብረመድህን ኃይሌ

አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው…

“ጨዋታው ጥሩ የሚባል ነው። ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ታግለናል። የድካማችንን ዋጋም አግኝተናል።

በሜዳቸው ቡድኑ እያሳየ ስላለው መሻሻል…

“ሥራ ሰርቶ ለውጥ ማምጣት ነው። ሁላችንም ሥራችንን በደንብ ሰርተን ነው መሻሻል ያሳየነው። በእግርኳስ ውጤት ለማምጣት ከዲሲፕሊን ጀምሮ ሥራን መስራት ያስፈልጋል። እነዛን አሟልተን ነው ሜዳ ላይ የተሻለ ለመሆን የሞከርነው። ተጫዋቾቻችን በደንብ እያረፉ እኛ የምንላቸውን እየሰሙ ነው ወደ ሜዳ የሚገቡት። መተባበር፣ መከባበር እና መረዳዳት ቡድናችን ውስጥ አለ። ይሄ ሁሉ ነገር ነው ውጤታማ ያደረገን።

ስለቡድኑ ደጋፊዎች…

“ሥራ ሰርተን ደጋፊያችን ጋር መጥተናል። ደጋፊው ደግሞ ሥራችንን አይቷል። ሥራችንን ካየ ምን ይፈልጋል? በትክክል መደገፍ ብቻ ነው ያለበት። እስከ መጨረሻ በጥሩ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በችግር ጊዜም አይዟችሁ ብሎ ከጎናችን ነበር።”

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን

ስለጨዋታው…

“ጨዋታው መጥፎ አይደለም። በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ ነበር። ነገር ግን ከምንፈልገው ነገር አንፃር ያሰብነውን አላገኘንም። ውጤቱም ጥሩ አልሆነም። ስህተቶች ነበሩብን። ስህተቶቻችንን ለቀጣይ ጨዋታ እናስተካክላለን።

በጨዋታው ጥሩ ስላልነበረው ክፍል…

“የተከላካይ መስመራችን ጥሩ የሚባል አልነበረም። በተወሰነ የራስ መተማመን የማጣት ነገር ይታይባቸው ነበር። ዕረፍት ላይ ይሄንን ለማስተካከል እና እነርሱን ለማረጋጋት ሞክረን ነበር ፤ ግን በሁለተኛውም አጋማሽ አልተስተካከለም።

ባለቀ ደቂቃ ግብ ስላስተናገዱበት ምክንያት…

“ጨዋታውን ለማሸነፍ ሙሉ አቅማችንን ማጥቃት ላይ አድርገን ነበር። በዚህ ሰዓት ጎል ገባብን። ለማረምም ጊዜ ስለሌለ ጨዋታውን አጥተነዋል።

ከጨዋታው ማግኘት ስለነበረባቸው ነገር…

“ከጨዋታው አቻ ይገባን ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ባንሆንም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻልን ነበርን። ከዚህ አንፃር አቻ ይገባን ነበር።”