ሪፖርት | ቡናማዎቹ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

ስድስት ግቦች በተስተናገዱበት የምሽቱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮ ኤሌክትሪክን 4-2 ረቷል።

በ8ኛ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድሬደዋ ከተማ ከተሸነፈበት ስብስቡ ማታይ ሉል እና ልደቱ ለማን በኃይሌ ገ/ተንሣይ እና ሔኖክ አየለ በመተካት ወደ ሜዳ ገብቷል። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በባህር ዳር ከተማ ከተረታበት ጨዋታ ኩዋኩ ዱሀ ፣ ዘነበ ከድር ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና አንተነህ ተፈራን በማሳረፍ በምትካቸው ገዛህኝ ደሳለኝ ፣ ራምኬል ጀምስ ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ጫላ ተሺታ አስገብቶ ለፍልሚያው ተዘጋጅቷል።

የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መንቀሳቀስ የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ገና በ3ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወርቁ በሞከረው ኳስ ቀዳሚ ለመሆን ቢጥሩም ውጥናቸውን ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ አምክኖታል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደግሞ የቡናን ጫና ለመከላከል ወደ ኋላ በማፈግፈግ ክፍተቶችን ለመዝጋት ሞክረዋል። በ12ኛው ደቂቃ ግን ናትናኤል ሰለሞን ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ሲያሻማው አምበሉ ስንታየሁ ወለጬ በግንባር ለማስቆጠር ጥሮ ዒላማውን ስቶበታል።

የሩብ ሰዓት ዋዜማው ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪ ሆነዋል። በዚህም በ14ኛው ደቂቃ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ በተቃራኒው የግብ ቋሚ ላይ የነበረው መሐመድኑር ናስር በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ ጋር አዋህዶታል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ካልታሰበ መንገድ መሪነታቸውን አሳድገዋል። በዚህም ኤሌክትሪኮች ከግብ ክልላቸው ኳስ ለመመስረት በመሞከር የግብ ዘቡ ዘሪሁን ታደለ ኳስ ለማቀበል ሲጥር ማቀበያውን መስመር የዘጋው ብሩክ በየነ ነክቶበት ሁለተኛ ጎል ተቆጥሯል።

ሁለቱ ግብ ያልበቃቸው ቡናማዎቹ ከደቂቃዎች በኋላም የቆመን ኳስ መነሻ ባደረገ አጋጣሚ ለሦስተኛ ግብ ቀርበው ነበር። ከቀኝ መስመር የተሻማው ኳስ በተከላካዮች ተጨራርፎ የደረሰው ብሩክ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወጥቶበታል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወዲያው ከመከላከል ወደ ማጥቃት አጨዋወት የተሸጋገሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ27ኛው ደቂቃ ለግብ ቀርበው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ስንታየሁ ወለጬ ከፀጋ ደርቤ የደረሰውን ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ አክርሮ ቢመታውም የግቡ ቋሚ ከግብነት ታድጎበታል። በቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ኤሌክትሪክ በተለይ በፀጋ አማካኝነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲጥር የተመለከትን ሲሆን ቡናዎች ደግሞ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የነበራቸውን ጫና ጋብ አድርገው ኳስን ማንሸራሸር ላይ ተጠምደው ነበር።

በ3-5-2 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ጨዋታውን እየከወኑ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ በመጠኑ ቀዝቀዝ ብለው ነበር። ይህ ቢሆንም ግን በ53ኛው ደቂቃ በመሐመድኑር ናስር አማካኝነት ሦስተኛ ጎል አስቆጥረው የጎል መጠኑን ከፍ አድርገዋል። በአንፃራዊነት በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት ኤልፓዎች በተደጋጋሚ የተጋጣሚን ሳጥን እየጎበኙ ነበር። ሦስተኛውን ግብ ካስተናገዱ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል የተሻማን ኳስ ሔኖክ አየለ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ በግንባሩ ግብ አድርጎታል። 60ኛው ደቂቃ ላይም ፀጋን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኢብራሄም ከግራ መስመር ጥሩ ኳስ ሞክሮ እስቄል ሞራኬ ባያወጣበት ሁለተኛ ግብ ያገኙ ነበር።

ቀስ እያለ እየተጋጋለ የመጣው የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ በ69 እና 71ኛው ደቂቃ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ጎሎች ተቆጥረውበታል። በቅድሚያም ከመስመር የተሻገረን ኳስ የቡና ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳት ተስኗቸው እግሩ ስር የደረሰው ልደቱ ለማ መዳረሺያው መረብ ላይ አድርጎታል። ከዚህ ግብ በኋላ በጨዋታው ህይወት የዘሩ የሚመስሉት ኤሌክትሪኮች ከደቂቃ በኋላ ግን ሳጥን ውስጥ ጥፋት ሰርተው የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶባቸዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ሮቤል ተክለሚካኤል በቀኝ እግሩ የቡና አራተኛ ግብ አድርጎታል።

ተስፋ ያልቆረጡት ኤሌክትሪኮች አራተኛውን ግብ ካስተናገዱ በኋላ በናትናኤል አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው አድኖባቸዋል። ኤሌክትሪኮች ግብ ፍለጋ በቁጥር በዝተው መውጣታቸውን ተከትሎ ቡናማዎቹ ያገኙትን የተከላካይ ጀርባ ቦታ ለመጠቀም በመጣር በ80ኛው ደቂቃ በሁለተኛው ጎል ባለቤታቸው ብሩክ አማካኝነት የማሳረጊያ ግብ ለማግኘት ጥቃት ቢፈፅሙም ኳስ የቀኙን የውጪ መረብ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል። ሔኖክ ድልቢም በ85ኛው ደቂቃ ሌላ ኳስ ወደ ግብ ልኮ ዒላማውን ስቶበታል። ኤልፓዎች በመጨረሻው ደቂቃ በአብነት እና ናትናኤል አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 4-2 አሸናፊነት ፍፃሜውም አግኝቷል።

ያጋሩ