መረጃዎች | 34ኛ የጨዋታ ቀን

የዘጠነኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የዕለቱ የመጀመሪያ መርሃግብር በአንድ ነጥብ ልዩነት ተለያይተው የተቀመጡትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኝ ይሆናል።

ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በመጨረሻ ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን ያሳኩት ሰራተኞቹ በአስራ ሦስት ነጥቦች በሰንጠረዡ በ6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ወልቂጤ ከተማን ያለ አምበላቸው ጌታነህ ከበደ ማሰብ ከባድ እየሆነ መጥቷል። እንደ ቡድን አስራ ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት ወልቂጤ ከተማዎች ሰባቱ (58%) የተገኙት ከጌታነህ ከበደ ነው። ከእስማኤል ኦሮ-አጎሮ በሦስት ግቦች አንሶ የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ተጫዋቹ ከዓመት ዓመት ብቃቱን ጠብቆ የመቀጠሉ ጉዳይ አድናቆትን የሚሻ ነው።

በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማሞች ቴዎድሮስ ሀሙን አሁንም በጉዳት የሚያጡት ሲሆን ግብ ጠባቂያቸው ጀማል ጣሰው ግን ከቅጣት ይመለሳል። ሌላኛው የቡድኑ የግብ ዘብ ሮበርት ኦዶንካራ ግን አሁንም ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አለማገገሙን ተከትሎ በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጥሯል።

በአዲሱ የውድድር ዘመን ሳይጠበቁ የተሻለ አጀማመርን ማድረግ የቻሉት ነብሮቹ ከተጋጣሚያቸው በአንድ ነጥብ በልጠው በሰንጠረዡ በ3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በመጨረሻ ጨዋታቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሀዋሳ ከተማን መደበኛው 90 ደቂቃ እስኪጠናቀቅ ድረስ 2-0 ሲመሩ ቢቆዩም በተጨማሪ ደቂቃዎች ባስተናገዷቸው ሁለት ግቦች በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ያጡበት መንገድ ፍፁም የሚያስቆጭ ነበር። በጨዋታው በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የነበረው የትኩረት ማጣት በቀጣይ እንዳይደገም በደንብ ትምህርት ይወስዱበታል ተብሎ ይታመናል።

በሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል ግርማ በቀለ አሁንም በቅጣት የማይኖር ሲሆን መለሰ ሚሻሞ ፣ ቤዛ መድህን እና እንዳለ ደባልቄ ደግሞ በጉዳት አይኖሩም፡፡ በተቃራኒው ባዬ ገዛኸኝ ፣ ፍቅየረሱስ ተወልደብርሃን እና ሳምሶን ጥላሁን ከጉዳት አገግመው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

በሊጉ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሥስቱ ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲጠናቀቁ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ የተቀረችውን አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል።

10 ሰዓት ሲል ጅማሮውን ለሚያደርገው ጨዋታ አባይነህ ሙላት በዋና ዳኝነት ተመድበዋል።

ወላይታ ድቻ ከ አርባምንጭ ከተማ

ከሁለት የጨዋታ ሳምንታት በፊት በሊጉ ግርጌ ላይ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገባቸውን ተከትሎ በስምንት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በመጨረሻ ጨዋታቸው ቡድኑ አዳማ ከተማን ሲረታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በኃይሉ ተሻገርን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ወጣቱ ዮናታን ኤልያስ በጨዋታው ከፍ ያለ ተፅዕኖን ማሳደር ችሏል። በጨዋታው አንድ ግብ ማስቆጠር የቻለው ዮናታን ለሁለተኛዋ ግብም መገኘት ምክንያት ነበር።

በክፍት ጨዋታ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ አሁንም ቢሆን ችግሮች ላሉበት ቡድኑ እንደ ዮናታን ላሉ ተጫዋቾች ተጨማሪ የጨዋታ ደቂቃዎችን በሜዳ ላይ እንዲያገኙ ማድረግ ምናልባት ለቡድኑ ማጥቃት ተስፋ ሊፈነጥቁ እንደሚችሉ የዮናታን ኤልያስ እንቅስቃሴ ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑን ተከትሎ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ሊያስቡበት ይገባል።

በወላይታ ድቻዎች በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ የሰነበቱት ፂሆን መርዕድ እና ስንታየሁ መንግሥቱ ወደ መደበኛ ልምምድ የተመለሱ ሲሆን በነገው ጨዋታ በአሰልጣኙ ከታመነባቸው ለመሰለፍ ዝግጁ መሆናቸው ሲረጋገጥ የንጋቱ ገብረስላሴ እና ዮናታን ኤልያስ የመሰለፍ ነገርግን አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ባለፈ እንድሪስ ሰዒድ ፣ ቢኒያም ፍቅሬ እና አንተነህ ጉግሳ ግን አሁንም በጉዳት ከስብስብ ውጭ ናቸው።

አርባምንጭ ከተማዎች በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ድላቸውን ካሳኩ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦችን ብቻ ያሳኩ ሲሆን አሁን ላይ በስድስት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪው ቡድን ከተከታታይ ፈታኝ መርሃግብሮች በኋላ የውድድር ዘመናቸውን ወደ መስመር ሊያስገቡባቸው የሚችሏቸው መርሃግብሮች ከፊታቸው ይገኛሉ። በብዙ መልኩ የአምናውን ቡድን ለመመሰል የቸገሩት አርባምንጭ ከተማዎች በፍጥነት ራሳቸውን ፈልገው ማግኘት ይኖርባቸዋል። በተለይም አምና በቡድኑ የጥንቃቄ መር አጨዋወት ውስጥ በመከላከሉም ሆነ በመልሶ ማጥቃቶች ወቅት ቁልፍ ሚናን ይወጣ የነበረው የቡድኑ አማካይ መስመር የዘንድሮ አበርክቶ ፍፁም መሻሻልን የሚሻ ነው።

በጨዋታው በአርባምንጭ ከተማዎች በኩል ከግብ ዘቡ አቤል ማሞ በስተቀር የተቀረው ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች 12 ጊዜ የተገናኙት ሲሆን በሰባቱ ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲፈፅሙ ወላይታ ድቻዎች አራት እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።

የምሽቱን ጨዋታ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።