ወልቂጤ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና የጨዋታ ሳምንቱን የመጀመሪያ ያለ ግብ የተጠናቀቀ አቻ አስመዝግበዋል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከለገጣፎ ለገዳዲ ሦስት ግብ እና ሦስት ነጥብ የወሰዱት ወልቂጤ ከተማዎች የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ የዛሬውን ጨዋታ ቀርበዋል። በዚህም ፋሲል አበባየሁ የተመስገን በጅሮንድን ቦታ በመያዝ ወደ ቀዳሚው አሰላለፍ መጥቷል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ባለቀ ደቂቃ ሁለት ጎል ተቆጥሮባቸው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ሁለት አቻ የተለያዩበትን ቀዳሚ አሰላለፍ ሳይለውጡ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ገና ከጅምሩ ጫና ፈጥረው ለመጫወት የጣሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ4ኛው ደቂቃ ስቴቨን ናያርኮ ከሳጥን ውጪ በሞከረው ኳስ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ፀጋዬ ብርሀኑ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሪችሞንድ ኦዶንጎ በአንድ ንክኪ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። በአንፃራዊነት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫና የበዛባቸው ወልቂጤዎች በሁለቱ ሙከራዎች መሀል ፋሲል አበባየሁ ሳጥኑ ጫፍ በመሆን በሞከረው ኳስ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ጥረዋል። በ12ኛው ደቂቃ ደግሞ በተደራጀ አጨዋወት የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ለአቡበከር ሳኒ አቀብሎት ወደ ሳጥን የተሻማውን ኳስ ብዙዓየሁ ሰይፉ ሊጠቀመው ሲል ፍሬዘር ካሣ ምቾት እንዳይሰማው በማድረግ ኳስ ወደ ውጪ እንዲወጣ አድርጓል።
አሁንም ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሀዲያዎች በ17ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ከመስመር ወደ መሐል ተስቦ በመግባት ያገኘውን ኳስ በውጪ እግሩ አክርሮ መትቶ መረብ ላይ ሊያሳርፍ ተቃርቦ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ወልቂጤዎች ምላል ለመስጠት ነቅለው በሚወጡበት ሰዓት ጌታነህ ላይ ጥፋት ተሰርቶ የተገኘውን የቅጣት ምት ራሱ ጌታነህ መትቶት ግብ ጠባቂው ፔፕ ሴይዶ አድኖበታል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የግብ ሙከራዎችን በማድረጉ ረገድ የተቀዛቀዘው የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ሲቆራረጡ እና አካላዊ ጉሽሚያዎች በዝተውበት ታይቷል። በአንፃራዊነት የሚያገኟቸውን የቆሙ ኳሶች ለመጠቀም ሲጥሩ የታዩት ወልቂጤዎች የአፈፃፀም ውስንነት ባይኖርባቸው ኖር የሀዲያን የቆመ ኳስ ደካማ መከላከል በመንተራስ ወደ መሪነት ሊሸጋገሩ የሚችሉባቸው ሁነቶች አምልጧቸዋል።
በ38ኛው ደቂቃ ግን በጥሩ የመስመር አጨዋወት ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ፋሲል አበባየሁ መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ የዘገየ የሳጥን ውስጥ ሩጫ ያደረገው ብዙዓየው ሞክሮት ወደ ላይ ባይወጣበት ኖሮ የመጀመሪያውን ጎል ያገኙ ነበር። አጋማሹ ተገባዶ በተጨመረው ደቂቃ ላይ የመጨረሻውን ሙከራ ብርሃኑ በቀለ ከቅጣት ምት አስመልክቶ ቡድኖቹ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደተጀመረ ሀዲያዎች እንደ ቀዳሚው 45 ጫና ፈጥረው መጫወትን መርጠዋል። አከታትለውም በሪችሞንድ ኦዶንጎ የግንባር ኳሶች ፋሪስ አላዊን ለመፈተን ጥረዋል። በተለይ ብርሃኑ ከቀኝ መስመር አሻምቶት የነበረው ኳስ በጋናዊው አጥቂ ወደ ግብነት ለመቀየር እጅግ የቀረበ ነበር። በ53ኛው ደቂቃ ደግሞ አክሊሉ ዋለልኝ ከሳጥን ውጪ ሦስተኛ ሙከራ አድርጎ ተመልሷል።
የአየር ላይ ኳሶች የበረከቱበት ፍልሚያው የጠሩ የግብ ዕድሎችን ማስተናገድ ብርቁ ሆኖ ነበር። በመጠኑ ደቂቃ በደቂቃ እየተነቃቁ የመጡት ወልቂጤዎች በተለይ አቡበከር በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል ያመዘነ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲጣጣሩ ነበር። ሀዲያዎች በበኩላቸው የአማካይ መስመሩ ላይ የቁጥር ብልጫ ወስደው ለመንቀሳቀስ እና በአንድ ሁለት ቅብብል የወልቂጤን ግብ ለመጎብኘት ሲጥሩ ታይቷል።
በአጋማሹ ግን ከ53ኛው ደቂቃ ሙከራ በኋላ ሌላ ለግብ የቀረበ ጥቃት የተስተናገደው በ82ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህም ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ ዳግም ንጉሴ በግንባሩ ሞክሮት ወጥቶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የጨዋታው እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ መክኗል። በዚህም ጌታነህ ከበደ ከግራ የሳጥኑ ክፍል ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታው የግብ ዘቡ ሰይዶ በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ ሰውነቱን አግዝፎ በመውጣት ዕድሉን አምክኖታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ፍፃሜውን አግኝቷል።