የአሠልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-0 ሀዲያ ሆሳዕና

👉”እኔ ጨዋታው ጥሩ ነበር ብዬ አልልም ፤ በሁለታችንም በኩል ጥሩ ነገር አልታየም” ገብረክርስቶስ ቢራራ

👉”ማሸነፍ የተሻለ ቦታ ላይ ያስቀምጠን ነበር ፤ ይህንን ዕድል ዛሬ አልተጠቀምንም” ያሬድ ገመቹ

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው…

እኔ ጨዋታው ጥሩ ነበር ብዬ አልልም። በሁለታችንም በኩል ጥሩ ነገር አልታየም። ይሄ ደግሞ የሆነው ሜዳው ምቹ ስላልሆነ ነው። እንደፈለግን እንድንጫወት አላመቸንም። እንደሚታወቀው የእኛ ቡድን ኳስ መስርቶ የሚጫወት ቡድን ነው። ከሜዳው ችግር አኳያ ግን ረጅም ኳስ ነበር ስንጫወት የነበረው። ምክንያቱም ብንቀባበል ኳሱ እየተበላሸ ራሳችን ላይ ችግር ከሚመጣብን ብለን ያዘዝነው ረጃጅም ኳስ እንድንጫወት ነው። በአጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ጨዋታ አይደለም።

ሜዳውን ስላለመዱበት ምክንያት…

ሜዳው የሚለመድ አይደለም። ሜዳው ላይ ብናድር እና ብንውል ሜዳውን አንለምደውም። ምክንያቱም የተመሰረትንበት የጨዋታ ዘዴያችን ቅብብል ስለሆነ። ረጅም ኳስ ለመጫወት ዛሬ ነው ያቀድነው። በተቻለ መጠን ረጅም ኳስ ለመጠቀም ሞክረን የተሻለ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረናል። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ብንጠቀም አሸናፊ እንሆን ነበር ፤ ብናሸንፍም ባናሸንፍም ግን ጨዋታው ለእኔ ጥሩ አልነበረም።

ያሰቡት የጨዋታ መንገድ ስኬታማ ስላልሆነበት ምክንያት…

ስንጠቀማቸው የነበሩ ረጃጅም ኳሶች እነርሱ ረጃጅም ተከላካዮች ጋር ነበር ሲደርሱ የነበሩት። ብዙ ደጋግመህ ያልሰራከው ነገር ለስህተት ይዳርግሀል።

ስለአቻ ውጤቱ ፍትሀዊነት…

እኛ የተሻሉ አማራጮችን አግኝተን ነበር። ባለቀ ደቂቃ እጅግ ለግብ ቀርበን ነው የሳትነው። ከእረፍት በፊት ደግሞ ከእነርሱ የተሻሉ ሁለት ኳሶችን ሞክረናል። እነርሱ ወደ ጎል የመጡበት መንገድ አልነበረም። እንደዚህም ሆኖ ማሸነፍ ነበረብን።

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው..

በፈለግነው መልክ አልተጠናቀቀም። ማሸነፍ የተሻለ ቦታ ላይ ያስቀምጠን ነበር። ይህንን ዕድል ዛሬ አልተጠቀምንም።

በተከታታይ ነጥብ መጣላቸው እና ከመሪዎቹ ስለመራቃቸው…

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አለን። ያን ተስተካካይ ጨዋታ የምናሸንፍ ከሆነ ከመሪው ጋር በዕኩል 18 ነጥብ ያስቀምጠናል።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጥሩ ስለማጥቃቸው እና በኋላ ስለመድከማቸው…

እኛ በመጀመሪያ 23 ደቂቃዎች ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻልንም። ያ እነሱን አነሳስቷቸዋል። በተደጋጋሚ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ማባከናችን እነሱን ተነሳሽነት እንዲያገኙ ነው ያደረጋቸውና ወደጨዋታው ገቡ። ከዛ በኋላ ዕኩል ተፎካካሪ ሆነን ነው እስከመጨረሻው የተጓዝነው።

ተጫዋቾችን በጉዳት ስለማጣታቸው…

ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። ተቀይረው የሚገቡትም ተጫዋቾች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው። እነዛ ተጫዋቾች ቢኖሩ ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ያደርገን ነበር። ከልምዳቸውም ካላቸውም አቅም በመነሳት ውጤታማ ያደርጉን ነበር። ቢሆንም እነዚህም በጣም ጠንካራ እና የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል ብዬ ነው የማስበው።