ሪፖርት | ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ የጦና ንቦቹ እና አዞዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

የወላይታ ድቻ እና አርባምንጭ ከተማ ፍልሚያ እንደ መጀመሪያው የዕለቱ ጨዋታ ቀልብን የሚገዛ ፉክክር ሳይደረግበት ያለግብ ተጠናቋል።

ምሽት 1፡00 ላይ የወላይታ ድቻና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ የጦና ንቦቹ በስምንተኛው ሳምንት አዳማ ከተማን 2-1 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሳሙኤል ተስፋዬ እና ዘላለም አባተ በደጉ ደበበ እና በኃይሉ ተሻገር ተተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። አዞዎቹ በበኩላቸው በስምንተኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር 1-1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ወርቅይታደስ አበበ እና መላኩ ኤልያስ በአካሉ አትሞ እና ሱራፌል ዳንኤል ተተክተዋል።

በስታዲየሙ እንደነበረው አየር ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እምብዛም ሳቢ አልነበረም። የግብ ሙከራዎችንም የሚያስተናግድ ያልነበረ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በረጃጅሙ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚልኳቸው ኳሶች በርክተው ታይተዋል። በአንፃራዊነት ከኳስ ጋር የተሻለ ጊዜ ሲያሳልፉ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች ቢሆኑም በአላማ የላይኛው ሜዳ ክልል ጥራት ያለው ቅንጅት ሲያሳዩ አልነበረም። ጨዋታውም የመጀመሪያ ሙከራውን በ21ኛው ደቂቃ አግኝቷል። እርሱም የግራ መስመር ተከላላዩ አናጋው ባደግ ከሳጥን ውጪ የሞከረው እና ዒላማውን የሳተው ሙከራ ነበር። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አርባምንጮች በጥሩ ሂደት የድቻ የግብ ክልል ቢደርሱም ለግብ የቀረበ የሚመስለው የመጨረሻ ኳሳቸው በተከላካዮች ተመልሷል።

ግማሽ ሰዓት እንዳለፈ በደቂቃ ልዩነት አዞዎቹ አስደንጋጭ ሁለት ቡጢዎችን ሰንዝረው ተመልሰዋል። በቅድሚያ አቡበከር ሻሚል ሳጥኑ ጫፍ ጥብቅ ኳስ መትቶ የግቡ ቋሚን ታኮ ሲወጣበት በቀጣይ ደግሞ ኤሪክ ካፓይቶ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ለመጠቀም ሲጥር ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ ራሱን ለጉዳት ዳርጎ ተቆጣጥሮታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ ራቅ ካለ ቦታ አሸናፊ ኤሊያስ ጥብቅ የቅጣት ምት ኳስ መትቶ ሁለተኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ቢስተናገድም ኳስ እና መረብ መገናኘት አልቻለም። አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቋል።

የማጥቃት ባህሪ ያለው ተጫዋች በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ለውጠው ያስገቡት ወላይታ ድቻዎች የመዓዘን ምትን መነሻ ባደረገ ኳስ ሀብታሙ ሙከራ ሰንዝሮላቸዋል። በተቃራኒው የመስመር አጨዋወታቸውን ለማሳደግ የመስመር ተጫዋች የቀየሩት አርባምንጭ ከተማዎችም ከደቂቃ በኋላ አጠፋዊ ምላሽ በተመሳሳይ በመዓዘን ምት ሞክረው ወጥቶባቸዋል። ከሁለት ደቂቃ በኋላም ካፓይቶ የአጋማሹን 3ኛ ሙከራ አድርጎ ተመልሷል። አሠልጣኝ መሳይ አማካይ መስመር ላይም ለውጥ በማድረግ የተሻለ ወደ ግብ መድረሻ መንገዳቸውን ያስተካከሉ ሲሆን በ55ኛው ደቂቃም የለውጣቸውን ፍሬ ለማየት ተቃርበው ለጥቂት መክኖባቸዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በመጠኑ ሻላ ያለ የመሰለው ጨዋታው በ62ኛው ደቂቃ ዘንድሮ የመጀመሪያ ጨዋታውን በቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ ገብቶ እያደረገ በሚገኘው ሳሙኤል ተስፋዬ አማካኝነት ሙከራ ተደርጎበታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት አማካዩ ኢማኑኤል ላርዬ የጨዋታውን የመጨረሻ ሙከራ ሰንዝሮ አሰልቺ የነበረው ጨዋታ ያለ ግብ ፍፃሜውን አግኝቷል።