የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጎል ተንበሽብሾ ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክም ሦስት ነጥብ ሸምቷል ቦሌ ክፍለከተማን ከአዲስ አበባ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

የሁለተኛ ሳምንት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የጀመሩት ረፋዱን አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደረጉት ጨዋታ ነበር፡፡ አጀማመሩ ተመጣጣኝ ሆኖ መታየት በቻለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ንግድ ባንኮች በሳሳው የመሀል ክፍላቸው ላይ ንቦኝ የንን በመለወጥ መጠነኛ ቅርፅን በመያዝ በተጋጣሚያቸው አዳማ ላይ ጫናን በማሳደር ጎል ወደ ማስቆጠሩ ገብተዋል፡፡ 29ኛው ደቂቃ ላይም በጥሩ የሜዳ ላይ የቅብብል ፍሰት የተገኘን ኳስ አምበሏ ልዛ አበራ ወደ ጎልነት ለውጣው ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡

ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በይበልጥ የተነቃቁት የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ንግድ ባንኮች አረጋሽ ከሰናይት ጋር በጥሩ ቅልጥፍና ተጫውታ በመጨረሻም ወደ ጎልነት ቀይራው የቡድኗን የጎል መጠን ማሳደግ ችላለች፡፡ ንግድ ባንክ የግብ ክልል ሲደርሱ ፍፁም ደካማ የነበሩት አዳማ ከተማዎች ተጨማሪ ጎል የኋላ መስመራቸው ላይ ከሚታየው ክፍተት መነሻነት ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ 41ኛው ደቂቃ ላይ መሠረቱን ከሰናይት እና እመቤት አድርጎ የደረሳት አጋጣሚ አረጋሽ ካልሳ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛ የሆነች ግብን ከመረብ አገናኝታለች፡፡

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ፈጣን ጎል አስተናግዷል። በዚህም ተቀይራ የገባችው መዲና ዐወል አራተኛ ጎልን ብስለቷን ተጠቅማ በማከል የቡድኗን የጎል መጠን አሳድጋለች፡፡ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩም አረጋሽ ካልሳ ለራሷ ሶስታ የሰራችበት ጎል ቡድኗም 5-0 አሸናፊ እንዲሆን ያደረገችን ግብ ከመረብ አዋህዳ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጨዋታ ምርጥ ሽልማትን አረጋሽ ካልሳ ወስዳለች፡፡

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ 8 ሰዓት ሲል በአርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ተደርጎ ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን አሳይቶን በኤሌክትሪክ የበላይነት ተደምድሟል፡፡ በሁለቱም የጨዋታ አጋማሾች ፍላጎት የታከለበትን ተደጋጋሚ የማጥቃት ኃይልን በተመለከትንበት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማዎች አብዛኛዎቹን የጨዋታ መንገድ በመልሶ ማጥቃት በተለይ ወደ መስመር ባዘነበለ አጨዋወት ለመጫወት ሲጥሩ ቢታይም በአንድ ሁለት መሀል ለመሀል ከአማካይ ክፍሉ በሚነሱ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ይታዩ የነበሩት ኤሌክትሪኮች የአርባምንጭ ተከላካዮች የአቋቋም ስህተትን በአጥቂ ተጫዋቾች ተጠቅሞ ለማስቆጠር በብርቱ ጥረዋል፡፡ ይህም ስህተታቸው 39ኛው ደቂቃ ላይ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ አጥቂዋ ትንቢት ሳሙኤል ይህን ክፍተት በመጠቀም ጎል አስቆጥራ ኤሌክትሪክን መሪ አድርጋለች፡፡

ከዕረፍት ጨዋታው ሲቀጥል አርባምንጮች አከታትለው የተጫዋች ቅያሪ በማድረግም ጭምር ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመመለስ ተግተው ቢጫወቱም መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠ ጭማሪ ላይ አርባምንጮች አሁንም ተከላካይ ክፍሉ እና ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም ዮሐንስ በሰሩት ያለ መናበብ ተቀይራ የገባችው ምንትዋብ ዮሃንስ ሁለተኛ ግብን በማከል ጨዋታው 2-0 ፍፃሜን አግኝቷል፡፡ ኤሌክትሪክም ተከታታይ የሆነ ድልን አስመዝግቧል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሰብለወንጌል ወዳጆ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የጨዋታው ኮከብ በመባል ተሸልማለች፡፡

10 ሰዓት ሲል ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች ቦሌ ክፍለከተማ እና አዲስ አበባ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር አስመልክቶን በመጨረሻም 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው አስር ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩበት የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ያሳዩ የነበሩት ቦሌዎች በሜላት አልሙዝ ጎል መሪ መሆን ቢችሉም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በታየባቸው መዘንጋት አማካዩዋ ቤተልሄም መንተሎ ለአዲስ አበባ አስቆጥራ ቡድኗን አቻ አድርጋለች፡፡ ጎል ለማስተናገድ ከተገደዱ በኋላ መቀዛቀዝ ውስጥ የገቡት ቦሌዎች ወደ መልበሻ ክፍል ጨዋታው ሊያመራ ጭማሪው ደቂቃ ላይ ሩታ ያደታ አዲስ አበባን ወደ 2ለ1 አሸጋግራለች፡፡

ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥን በማድረግ ቦሌዎች ሙሉ የጨዋታ ብልጫን ወስደው በመጫወት በመጨረሻም ወደ አቻነት ያሸጋገረቻቸውን ግብ 80ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ወደ ሜዳ በገባችው ምርጥነሽ ዮሃንስ አማካኝነት 2-2 ሆነው ጨዋታው ተገባዷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ስርጉት ተስፋዬ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተመርጣለች፡፡