የአሠልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-0 አርባምንጭ ከተማ

👉”ፍልሚያው ከነበረው መንፈስ አንፃር አቻ መውጣታችን ተገቢ ነው ብዬ ነው የማስበው” ፀጋዬ ኪዳነማርያም


👉”ብናሸንፍ መልካም ነበር ፤ ግን አልተሳካም ለቀጣይ ሰርተን እንመጣለን” መሳይ ተፈሪ

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ረጃጅም ኳሶች የበዙበት ነበር። ብዙ የኳስ ፍሰት የታየበት አይደለም። እነሱ በሁለት አጥቂ ነው ሲጫወቱ የነበሩ ፤ የሚገኙ ኳሶችን ሳጥን ውስጥ በመጣል በሁለተኛ ኳስ ተጠቃሚ ለመሆን ነው ጫና ሲፈጥሩብን የነበር። የመሃል ተከላካያችን ብቻ ሳይሆን የተከላካይ አማካያችንም አጭር ነው እና በሁለተኛ ኳስ ለመጠቀም ነበር ያሰቡት። እኛም ተቃራኒ አጨዋወት ለመምረጥ አልቻልንም ፤ ኳሱን ይዘን መጫወት አልቻልንምና በአብዛኛው በተመሳሳይ በረጅም ኳስ ነው ለመጫወት የሞከርነው። ውጥረት የነገሠበት ጨዋታ ነበር በነጥብ ደረጃም ተመሳሳይ ስምንት እና ስድስት ነጥብ ይዘን ስለገባን በደረጃ ሰንጠረዡም እንዳንነጣጠቅ ጥንቃቄ እያደረግን ነው የምንሄደው። አብዛኛው የእኛ ቡድን ውስጥ እንደነቢንያም ፣ ዘላለም ፣ መሳይ ፣ አበባዓየሁን የመሳሰሉትን ወጣቶች ነው ወደሜዳ እያስገባን ያለነው። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ከሜዳ እየራቁብን ነው ፤ ጉዳት እያስቸገረን ነው። ሲጠቃለል ግን ፍልሚያው ከነበረው መንፈስ አንጻር አቻ መውጣታችን ተገቢ ነው ብዬ ነው የማስበው። ”

ጨዋታው ሳቢ እንቅስቃሴ ስላለማሳየቱ….

ጨዋታው በታክቲክ የታጠረ ነበር ፤ የደርቢነት ስሜት አለው። በነጥብም  አንዳችን በአንዳችን የበላይነት እንዳይወሰድብን ጥንቃቄ እያደረግን ነበር የተጫወትነው። በአብዛኛው የመከላከያ ፍላጎት ነበር በሁለታችንም ሲንፀባረቅ የነበረው ፤ የፈጠራ ጨዋታዎች ብዙ የታዩበት አልነበረም። በረጃጅም ኳሶች የታጠረ ስለሆነ የሚሰነጠቁ ኳሶች የነበሩበት አልነበረም። የአየር ላይ ኳስ ያሸነፈ ነበር የሚያሸንፈውና ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ስንታየሁን ቀይረን ያስገባነው ከእንደዚህ ዓይነት አጨዋወት ተጠቃሚ ለመሆን ብለን ነበር። ከጨዋታው ተመጣጣኝነት አንጻር አቻ ተገቢ ነው ብዬ ነው የማስበው።

በአንጻራዊነት ወደኋላ ስለማፈግፈጋቸው…

እኛ ሰባተኛ እነሱ ስምንተኛ ጨዋታችንን ነው ያደረግነው። ከቀሪ ጨዋታዎቻችን አንጻር ነው ታሳቢ የምናደርገው። ቀጣይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነው ያለን ፤ ስለዚህ አርባምንጭ ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዳይወሰድብን ጥንቃቄ እያደረግን ነበር። ከነበረን የተጫዋች ስብስብ አንጻር ውጤቱ ተገቢ ነው።

መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

በጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የጎል አጋጣሚዎችን ፈጥረናል፡፡ ሁለተኛው ላይ ቀጥተኛ ኳስ ተጠቅመው በተወሰነ መልኩ ጫና ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ እኛም እንደዚሁ በሁለተኛ ኳስ ለመውጣት ጥረት አድርገናል፡፡ ብናሸንፍ መልካም ነበር ግን አልተሳካም ለቀጣይ ደግሞ ሰርተን እንመጣለን፡፡

ይቆራረጡ ስለ ነበሩ ኳሶች…

በተወሰነ መልሱ ሁለተኛ አርባ አምሰት ላይ መቆራረጥ ነበር፡፡ መጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ ኳሶች ነበሩ። ቢውልድ አፕ ተደርጎ ሲሄዱ የነበሩት ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ግን የእነርሱ መቀባበል በተወሰነ መልኩ በተረጋጋ ኳሶችን ለመመስረት ለማድረግ በተወሰነ ቻሌንድ ነበረው ፣ ጫና ለማድረግ ጥረት ያደርጉ ስለነበር ሁለተኛውን አማራጭ ስንጠቀም ነበር፡፡

ስለ ድሬዳዋ ቆይታ…

ከባህር ዳሩ የተሻለ ቆይታ በቀጣዩ ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሚቀሩ ነገሮች አሉ። በቀጣይ እነዛን አሻሽለን ጨምረን እንጠብቃለን። ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን ድሬዳዋ ላይ፡፡

ሁለቱን ቡድኖች ከማሰልጠኑ ጋር ስለተያያዘ ስሜት…

የተለየ ነገር አይኖርም። ረጅም ዓመት ነው በድቻ ቤት ያገለገልኩት። አሁን ደግሞ ለአርባምንጭ ከነማ ክብር አለኝ። ብዙ ነገር ያሳለፍኩበት ነው፡፡ እንግዲህ ዕኩል ለዕኩል ወጥተናል፡፡