የ9ኛው ሳምንት ማሳረጊያ በሆኑት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አሰናድተናል።

ፋሲል ከነማ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

ለፌደራል ዳኛ ብርሀኑ መኩሪያ የመጀመሪያ በሚሆነው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ መነሻቸው ከተለያየ ደረጃ ላይ ቢሆንም ወቅታዊ አቋማቸው እንዳሰቡት ያልሆነላቸው ፋሲል እና ለገጣፎን ያገናኛል።

ከውድድሩ አስቀድሞ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ፋሲል ከነማዎች ነገ ሰባተኛ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የእስካሀኑ የቡድኑ ጉዞ ግን አመርቂ ባለመሆኑ ራሱን ከሰንጠረዡ ወገብ በታች እንዲያገኘው ሆኗል። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያሳካው ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረታበት ጨዋታ በኋላ በሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ እና አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካት ችሏል።

ከብዙዎች ግምት ውጪ ጥሩ አጀማመር አድርጎ የነበረው ለገጣፎ ለጋዳዲ በበኩሉ አምስት ሽንፈቶችን በማስተናገድ በሰንጠረዡ ግርጌ ተቀምጧል። 15 ግቦችን ለማስተናገድ የተገደደው ቡድኑ የመጨረሻ ግቡን ካስቆጠረም አራት ዘጠና ደቂቃዎች አልፈዋል።

መርሐግብሩ ከስብስብ አንፃር እንዲሁም ከሰሞኑ ተጋጣሚዎቹ አንፃር ለፋሲል ከነማ ወደ አቋሙ የመመለሻ ዕድል የሚሰጥ ይመስላል። ሆኖም ግን ጨዋታው ሁለቱም በተጋጣሚዎቻቸው ዘንድ እንደቡድን ያጡትን አስፈሪነት መልሶ ለማግኘት የሚደረግ ይመላል። ለገጣፎ ለገዳዲ በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ ያሳየው በራስ መተማመን በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ላይም መደገም በተጋጣሚዎቹ ቀላል ግምት እንዳይሰጠው አድርጓል። ይህ መሆኑ በየጨዋታው ከባድ ፈተና እንዲገጥመው እና በሂደት ከውጤት እንዲርቅ ቢያደርገውም እንደነገ ዓይነት ትልልቅ ተጋጣሚዎችን ማሸነፍ መቻል ካለበት የዉጤት ቀውስ የመስፈንጠሪያ ዕድልን ይዞለት ሊመጣ ይችላል። ከዚህ በተለየ መንገድ ቢሆንም ፋሲል ከነማ ከጨዋታ አስቀድሞ በተጋጣሚዎች ላይ የሚወስደውን የሥነልቦና የበላይነት እያጣ ይመስላል። ይህም ሜዳ ውስጥ ቡድኖች አፈግፍገው እንዲቀርቡት እና እንቅስቃሴውን በራሱ መንገድ ለማስኬድ ይችልበት የነበረውን መንገድ አሳጥቶታል። ሁኔታውን ቀልብሶ ወደ አሸናፊነት መንፈስ ለመመለስ ደግሞ ከነገው ጨዋታ የተሻለ ዕድል ያለው አይመስልም።

የፋሲል ከነማው ሀብታሙ ተከስተ አሁንም ከቡድኑ ጋር የሌለ ሲሆን ሱራፌል ዳኛቸው እና ይሁን እንዳሻውም ልምምድ ቢጀምሩም የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ በለገጣፎ ከገዳዲ በኩል ያለውን የቡድን ዜና ለማግኘት ያረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።

ባህር ዳር ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በሰንጠረዡ የተለያየ ክፍሎች ላይ የሚገኙት ባህር ዳር እና አዳማ በተራራቀ ወቅታዊ አቋም ላይ ሆነው ነገ ምሽት ፌደራል ዳኛ ኢሳይያስ ታደሰ ከሁለት ዓመታት በኋላ በሚመለሱበት ጨዋታ ይፋለማሉ።

ባህር ዳር ከተማ ከከፍተኛ ሊጉ ከመጣ በኋላ በተሻለ ወጥነት ወደ ሰንጠረዡ አናት እየተጠጋ ያለበት ጊዜ ላይ ይገኛል። ዘንድሮ ካሳካው የመጀመሪያ ተከታታይ ድል በኋላ ለነገው ጨዋታ የሚቀርበው ቡድኑ በእነዚሁ ሁለት ድሎቹ ከተለያዩ አንስት ተጫዋቾች ስድስት ጎሎችን ማግኘት ችሏል።

አዳማ ከተማ አሁን ላይ ካሉት ሰባት ነጥቦች ውስጥ ስድስቱን ያሳካው በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች መሆኑ ስላለበት ወቅታዊ አቋም ይናገራል። ቡድኑ ደካማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ካለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የመጨረሻዋን ነጥብ ሲያገኝ በመጨረሻ ጨዋታዎች በወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ሽንፈት አግኝቶታል።

ባህር ዳር ከተማ መድን እና ቡናን የረታበት አቀራረብ ስለነገውም የሚነግረን ይመስላል። ከመድን ጋር የተጋጣሚውን ጠንካራ የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ በማገድ እና ብልጫ በማውሰድ ላይ ሲመሰረት ከቡና ጋር ደግሞ ተጋጣሚው ከኋላ ኳስ መስርቶ እንዳይወጣ በማድረጉ ላይ አተኩሮ ታይቷል። በሁለቱም አጋጣሚዎች ስኬታማ የሆኑት የጣና ሞገዶቹ ነገ በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርተው ፈጣን ጥቃቶችን በሚሰነዝሩበት አቀራረብ ወደ ሜዳ መግባትን አልይም የአዳማ ከተማን ድክመት አልመው መጀመርን ያስቀድማሉ የሚለው ይጠበቃል። በወላይታ ድቻው ሽንፈት የመጀመሪያ አጋማሽ ከአጨራረስ ድክመት ውጪ መጥፎ ያልነበሩት አዳማ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ያሳዩት ድክመት የነገ አንዱ ስጋታቸው ሊሆን ይችላል። ለተጋጣሚው አጨዋወት ምላሽ ከሚሰጥ ቡድን ጋር በጨዋታው የተወሰነ ክፍል ትኩረትን ማጣት ዋጋ ሊያስከፍል የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ሆኖም የአዳማ የፊት መስመር ተሰላፊዎች አልፎ አልፎ ግለሰባዊ ስህተቶች የሚታይበት የባህር ዳር የኋላ ክፍልን የመፈተን አቅም እንዳላቸውም መዘንጋት የለበትም።

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከባህር ዳር ከተማ ብቸኛው ጉዳት ላይ የሚገኝ ተጫዋች ሲሆን አደም አባስ ከጉዳት አይቮሪኮስታዊው ግብ ጠባቂ ቴፒኒ አልዛየር ደግሞ ከሀገሩ ተመልሰዋል። በአዳማ ከተማ በኩል ከሚሊዮን ሰለሞን ጉዳት በተጨማሪ ጀሚል ያዕቆብ እና አማነኤል ጎበና መጠነኛ ጉዳት ያለባቸው ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ ለነገ መድረሱ አጠራጣሪ ቢሆንም መሻሻል እያሳየ መሆኑን ሰምተናል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ከተገናኙባቸው ስድስት ጨዋታዎች አራቱ በባህር ዳር ከተማ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ አንዴ ነጥብ ተጋርተው አዳማ አምና አንድ ድል አሳክቷል። በግንኙነታቸው ባህር ዳር ከተማ ሰባት አዳማ ከተማ ደግሞ አንድ ግቦች አሏቸው።

ያጋሩ