👉”ሙሉ ስብስባችን ሲኖር ደግሞ ከዚህም የተሻለ ማድረግ እንችላለን” ኃይሉ ነጋሽ
👉 “ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ትኩረት እያጣን በመሄዳችን ግቦች ተቆጥረውብናል” ጥላሁን ተሾመ
አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ
ስለጨዋታው…
ጨዋታው ጥሩ ነበር። ዛሬ ኳስ ይዘን ለመጫወትና ለማሸነፍ ነበር የመጣነው። ተጫዋቾቼ ይሄንን ለማድረግ ሞክረዋል ፤ ግን ትንሽ ጭንቀት ነገር ይታያል። ይሄም የሆነው ከውጤት ፍለጋ ነው። ይህ ደግሞ የሚስተካከለው በውጤት ነው።
በመጀመሪያው አጋማሽ ስለመቸገራቸው…
ይህ የሆነው በተጋጣሚ ጥንካሬ ሳይሆን በእኛ ድክመት ነው። ከራስ መተማመን ጋር ይገናኛል። ቅድም እንዳልኩት ከውጤት ማጣት የተነሳ የምታጣው መተማመን ይኖራል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ይሄንን ተነጋግረው የተሻለ ነገር ሰርተን ሦስት ግቦችን አስቆጥረን ወጥተናል።
ያደረጉት የተጫዋች ለውጥ ስኬታማ ስለመሆኑ…
እውነት ነው። ስብስባች ውስጥ ብዙ ጉዳት አለ። ከነጉዳታቸውም የሚጫወቱ ተጫዋቾች አሉ። ሙሉ ስብስባችን ሲኖር ደግሞ ከዚህም የተሻለ ማድረግ እንችላለን። ተቀይረው ከገቡት ሱራፌል ከጉዳት የመጣ ነው። ከጉዳት እንደመምጣቱ እንቅስቃሴው ጥሩ ነበር። ከእርሱ በተጨማሪም ናትናኤልም ጥሩ ተንቀሳቅሶ ግብ አስቆጥሯል።
አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ
ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነበር። በሁለተኛውም አጋማሽ በእንቅስቃሴም የሳትናቸውም ጎሎች ነበሩ። ፋሲል ጠንካራ ቡድን ነው ፤ ከትልቅ ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው። ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ትኩረት እያጣን በመሄዳችን ግቦች ተቆጥረውብናል። የእኛው ስህተቶች ናቸው። የሚገቡብን ጎሎች ተቃራኒ ተጭኖን ሳይሆን እኛ የምንሰራቸው ስህተቶች ናቸው።
አቻ አስበው ስለመግባታቸው…
የመጀመሪያ ጨዋታችን አቻ ነው። አቻውን ካረጋገጥን በኋላ ነው ማግባት የምንችለው። ይህንኑ ነው ለተጫዋቾቼ የነገርኳቸው ፤ የሚችሉትን አድርገዋል። ወጣቶች በመሆናቸው ከ70 ደቂቃ በኋላ ትኩረታቸው እየወረደ ማድረግ የሚገባቸውን አላደረጉም ፤ ይህ ዋጋ አስከፍሎናል። ያው ከትልቅ ቡድን ጋር ተጫውተን ተሸንፈናል።
በሊጉ ስለመቆየታቸው…
በሊጉ መቆየት ገና ነው። ብዙ ጨዋታዎች አሉ። እሱም ብቻ ሳይሆን ተቀራራቢ ነጥቦች ናቸው ያሉት። ምንም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለም። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ መስተካከል ያለበትን አስተካክለን የተጨዋቾቻችንን ሞራል ጠብቀን ወደ ፊት የምንሄድ ይመስለኛል።
ስለካርሎስ ዳምጠው አጨራረስ ብቃት…
ካርሎስ ብዙ ጨዋታዎች ላይ አላገባም። ያለው እንቅስቃሴ የተሻለ ነው ፤ ጎል ላይ ይደርሳል። ስራ ይፈልጋል ፤ ካርሎስ ላይ የአዕምሮ ስራ መስራት ይኖርብናል። አለማግባቱን ብቻ ነው የሚያስበው ስህተቱን ብቻ ነው የሚያሰላስለው። ስለዚህ ገንብተነው የተሻለ ተጫዋች ይሆናል ፤ አቅም አለው። የተሻለ ተጫዋች መሆን ይችላል።