ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ በአሸናፊነት ግስጋሴያቸው ቀጥለዋል

በጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ ባህር ዳር ከተማ አዳማ ከተማን አንድ ለምንም ረቷል።

ምሽት 1፡00 ላይ የባህር ዳር ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ የጣና ሞገዶቹ በስምንተኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን 3-1 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ተስፋዬ ታምራት ፣ ፍጹም ጥላሁን እና ፋሲል አስማማው በፈቱዲን ጀማል ፣ ኦሴ ማውሊ እና ሀብታሙ ታደሰ ተተክተዋል።

አዳማዎች በበኩላቸው በስምንተኛው ሳምንት በወላይታ ድቻ 2-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሰዒድ ሀብታሙ ፣ ደስታ ዮሐንስ ፣ አብዲ ዋበላ ፣ ዳንኤል ደምሱ ፣ ዳዋ ሆቴሳ እና አቡበከር ወንድሙ የኩዋሜ ባህ ፣ ጀሚል ያዕቆብ ፣ ታዬ ጋሻው ፣ ፍሬድሪክ ሀንሰን ፣ አሜ መሀመድ እና ቦና ዓሊን ቦታ ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና ከጅምሩ ጥሩ ፉክክር ማሳየት ጀምሯል። ገና በ5ኛው ደቂቃም የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተደርጎ የመጀመሪያ ጎል ተቆጥሯል። በዚህም ዱሬሳ ሹቢሳ ፍጥነቱን ተጠቅሞ አፈትልኮ በመውጣት ያገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አሳርፎት ቡድኑን መሪ አድርጓል። 

14ኛው ደቂቃ ላይም በአዳማ ተጫዋቾች የቅብብል ስህተት እግሩ ስር ኳስ የደረሰው የግቡ ባለቤት ዱሬሳ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ግብ ቢሞክረውም አዲስ ተስፋዬ የአጋሮቹን ስህተት በጥሩ ሸርተቴ አርሞታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የግብ ዘቡ ሰዒድ ሀብታሙ አጥቂው ፋሲል አስማማው ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘ የቅጣት ምት ሲመታ ፉዐድ ፈረጃ አግኝቶት ተጨማሪ ግብ ለማድረግ ሞክሮ ወጥቶበታል።

ፈጣኖቹን የባህር ዳር አጥቂዎች መቆጣጠር የከበዳቸው አዳማዎች በ19ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም አድናን ረሻድ ከዳዋ ሁቴሳ የተቀበለውን ኳስ ከርቀት ቢመታውም ዒላማውን ስቶበት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ግማሽ ሰዓት ሳይሞላ አጥቂ እና የአጥቂ አማካያቸውን በጉዳት ከሜዳ ቀይረው ያስወጡት ባህር ዳሮች በ29ኛው ደቂቃ ፍፁም ጥላሁን ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት በላከው እና ፉዐድን ቀይሮ የገባው የአብስራ ተስፋዬ በሞከረው አጋጣሚ ሰዒድን ፈትነው ተመልሰዋል።

አጋማሹ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ራሱን ነፃ አድርጎ ቆሞ የነበረው ዊሊያም ሰለሞን ቡድኑን አቻ ማድረጊያ ኳስ ከመስዑድ መሐመድ ተቀብሎ ቢመታም ለጥቂት የቀኙን ቋሚ ታኮ ወጥቶበታል። የመሐል ዳኛው ኢሳይያስ ታደሠ የጨመሩት ደቂቃ ማብቂያ ላይ ደግሞ ባህር ዳር ከቀኝ መስመር የተሻገረን ኳስ ተከላካዩ አዲስ አፀዳለው ብሎ ወደ ራሱ ግብ አቅጣጫ በመታው አጋጣሚ ሁለተኛ ግብ ለማግኘት እጅግ ቀርቦ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ አማካይ እና አጥቂ መስመራቸው ላይ ለውጥ ያደረጉት አዳማዎች በጨዋታው የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሲጥሩ ነበር። ባህር ዳሮችም የአዳማን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመቀማት ጥረቶችን በማድረግ በዋናነት ተጎድቶ የወጣው ፋሲልን ቀይሮ የገባው ኦሴ ማውሊን ዒላማ ያደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች ሲልኩ ነበር። በ65ኛው ደቂቃ ላይም ማውሊ በተጠቀሰው አጨዋወት የተቀበለውን ኳስ መትቶ ወጥቶበታል። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ አድናን ሳጥኑ መግቢያ ላይ ሙከራ ልኮ ግብ ጠባቂው ፋሲል ተቆጣጥሮበታል።

የአቻነት ጎል ፍለጋቸውን የቀጠሉት አዳማዎች በ77ኛው ደቂቃ ቢኒያም አይተን ከቀኝ መስመር አሻምቶት ዊሊያም በሞከረው እና በተከላካዮች ተመልሶ ፍሬድሪክ አንሳ በመታው ኳስ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ አዳማ እጅግ ለግብ ቀርበው መክኖባቸዋል። በዚህም አሜ መሐመድ ከቀኝ መስመር አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ፋሲል አድኖበታል። በድጋሜ በጭማሪው ደቂቃ ቢኒያም ከተቃራኒ አቅጣጫ ሌላ ሙከራ ልኮ ውጥኑ ሳይሰምር ቀርቷል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ያጋሩ