የአሠልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-0 አዳማ ከተማ

👉”ተጫዋቾቻችን ያላቸውን ከአቅማቸውም በላይ በመስጠት ዛሬ ሦስት ነጥብ ይዘን እንድንወጣ አድርገዋል” ደግአረገ ይግዛው

👉”በዚህ ጨዋታ ቢያንስ አቻ መውጣት ይገባን ነበር ብዬ ነው የማስበው” ይታገሱ እንዳለ

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው በጣም ቆንጆ ነበር፡፡ አዳማ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ከመሸነፍ የመጣም እንደ መሆኑ መጠን ጠንካራ ፍልሚያ እንደሚጠብቀን እናውቅ ነበር ፣ ሆኖም ግን ተጫዋቾቻችን ያላቸውን ከአቅማቸውም በላይ በመስጠት ዛሬ ሦስት ነጥብ ይዘን እንድንወጣ አድርገዋል፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ በሁለተኛው ተቀዛቅዞ ስለቀረቡበት ሁኔታ…

በነበረን ብልጫ ብዙ የግብ ዕድሎችንም ፈጥረን ነበር መጠቀም አልቻልንም፡፡ ሆኖም ግን ሁለተኛው አርባ አምስት ከመግባታችን በፊት አስገዳጅ ለውጦችን እንድናደርግ የተገደድንበት ሀኔታ ነበር፡፡ እሱ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ይዘን የገባነውን ዕቅድ እንዳንተገብር ችግር ፈጥሮብናል፡፡ ሁለቱም ተጫዋቾችን በመጀመሪያ ምርጫ ውስጥ ነበሩ ጥሩ በሚንቀሳቀሱበት ሰዓት ነበር ጉዳት ያስተናገዱት ፣ ያ አንዱ ችግር ነበር በተረፈ ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ውድድሩ እንዳየህው ጫና ያለበት ነው ፣ ተጫዋቾቻችን ያንን ጫና ተቋቁሞ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት የሄዱበት ርቀት እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ የመጀመሪያው አርባ አምስትን እና ሁለተኛው አርባ አምስትን ስናየው ፣ በዕርግጥ የመጀመሪያው አርባ አምስት ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል የምንደርስበት ብልጫውን ተቆጣጥረን ጨዋታውን የተጫወትንበት ቢሆንም ሁለተኛው አርባ አምስት ደግሞ የተገኘውን ጠብቆ ጥንቃቄ ያለውን ጨዋታ ለመጫወት ነው የሞከርነው፡፡

ስለ ፉአድ ፈረጃ እና ፋሲል አስማማው ጉዳት…

ከሜዳ እየወጣው ነው ፤ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማወቅ አይቻልም። ተስፋ አደርጋለሁ ለቀጣይ ጨዋታ ይደርሱልናል። በተረፈ ግን ቀጣይ ባሉ እንቅስቃሴዎች እንደዚህ ዓይነት ጉዳቶችን ልናስተናግድ እንደምንችል የሚጠበቅ ነው ጤናውን በቶሎ እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡

ቡድኑ ድሬዳዋ ላይ ስለ መሻሻሉ…

ትልቁ ነገር የተጫዋቾቻችን ጥረት ነው፡፡ ተጫዋቾቻችን ለእያንዳንዱ ጨዋታ ተገቢውን ክብር እና ትኩረት በመስጠት ዘጠና ደቂቃውን ውጤት ይዞ ለመውጣት የሚሄዱበት መንገድ ያለው የቲም ስፕሪት እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ በተረፈ ድሬዳዋ ካደረግናቸው ጨዋታዎች ሦስቱንም በማሸነፍ ዘጠኝ ነጥብን ይዘን ወጥተናል፡፡ ይህ ማለት የመጨረሻ ግባችን አይደለም። ከፊታችን ብዙ ጨዋታዎች አሉ ከ22 ያላነሰ ጨዋታዎች ከፊታችን ይጠብቀናል። እና ፈታኝ ጉዞ እንዳ አውቀን አሁንም በቀጣይ የተሻልን ሆነን ለመገኘት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡


አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

በመጀመሪያ ደቂቃዎች በተቆጠረብን ጎል ነጥብ ጥለን ወጥተናል። ግን ጨዋታው ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው።

ስለ ውጤቱ ተገቢነት…

እሱን የሚያውቀው ተመልካች ነው። ፍርድ መስጠት የሚችለው እና ኃላፊነት የሚወስደው ተመልካች ነው። ከዕረፍት በኋላም ይሁን ከዕረፍት በፊት ባለን ነገር ለመጫወት ሞክረናል። ይሄ ውጤት ይገባናል ብዬ እንደ አሰልጣኝ መናገር ይከብደኛል። ባህርዳር ትልቅ ቡድን ነው። እነሱም የራሳቸውን አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ ፤ ግን በዚህ ጨዋታ ቢያንስ አቻ መውጣት ይገባን ነበር ብዬ ነው የማስበው።

በመጀመሪያ ደቂቃ ግብ ስላስተናገዱበት ምክንያት…

አዳዲስ ተጫዋቾችን ነው እየሞከርን ያለነው። ተከላካይ ላይ ምንም የተረጋጉ ነገሮች የሉም። በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች መከላከላችንን በአዲስ እያደራጀን ነውና በአራት ደቂቃ ውስጥ የገባብን ጎል እንደሚታየው ነው። ቋሚ ተከላካይ የለንም። በህመም እና በተለያዩ ነገሮች እና አንድ ላይ ልናገኛቸው ስላልቻልን በዛ ምክንያት ነው።

ውጤት እየራቃቸው ስለመሆኑ…

የተጎዱት ተጫዋቾች መጥተው በውጤታችን ከዚህ የተሻለ ሆነን እንደምንጨርስ እና የተሻለ ቡድን እንደሆነ ይገባኛል። ውጤቱ እየራቀ ነው ምንም ጥርጥር የለውም ፤ ጠንክረን መሥራት ያስፈልጋል። አንዳንዴ የሚመጣውን መቀበል ነው።