የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ በጎል ሲንበሸበሽ መቻልም ድል አድርጓል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥል ሀዋሳ ከተማ ከግማሽ ደርዘን በላይ ግብ አስቆጥሮ ሲያሸንፍ መቻልም ሦስት ነጥብ አሳክቷል፡፡ የይርጋ ጨፌ ቡና እና የልደታ ክፍለከተማ ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

4 ሰዓት ሲል መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኘው ጨዋታ ቀዳሚው የዕለቱ መርሀግብር ነበር። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሙሉ በሙሉ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች ከሁሉም የሜዳው ክፍል በሚነሱ ኳሶች ጥቃቶችን ለመሰንዘር በተደጋጋሚ ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ በተለይ ደግሞ ከመስመር በሚነሱ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚጥሩበት ሂደት ቶሎ ቶሎ በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ደርሰው እንዲያጠቁ ማድረግ ቢያስችላቸውም የሚያገኙትን በአግባቡ ከመጠቀሙ አንፃር ግን ደካሞች ነበሩ፡፡ በጥብቅ መከላከል በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ይተጉ የነበሩት የአሰልጣኝ ራውዳ ዓሊው ቅዱስ ጊዮርጊስ 33ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዮች በሰሩት ስህተት የተነሳ ሴናፍ ዋቁማ ግብ አስቆጥራባቸው መቻል መሪ መሆን ችሏል፡፡

ጨዋታው 37ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመቻሏ አማካይ ማዕድን ሳዕሉ ሜዳ ላይ ያለ ምንም ንክኪ በመውደቋ ምክንያት አስደንጋጭ አደጋ አስተናግዳ የነበረ ሲሆን በስታዲየሙ አምቡላንስ አለመኖሩን ተከትሎ በሰው ኃይል ተሸክመው ሲያወጧት ለመታዘብ ችለናል፡፡ በሀገሪቱ ትልቁን ቦታ በሚወስደው የሴቶች የሊግ ውድድር ላይ አምቡላንስ አለመኖሩ በስታዲየሙ የታደሙ ተመልካቾችን ለተቃውሞ የዳረገ ሲሆን አወዳዳሪው አካልም አፋጣኝ የሆነ ምላሽ በዚህ ላይ መስጠት እንዳለበት ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ቀጥሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ብልጫን ወስደው በመንቀሳቀስ ግብ ለማስቆጠር የመቻል የግብ ክልል ዙሪያ ሲያንዣብቡ ቢሰነብቱም ጎል እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ጨዋታው በመከላከያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የመከላከያዋ አማካይ ሳራ ኪዶ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተሸልማለች።

ሁለተኛ መርሀግብር የነበረው የሀዋሳ ከተማ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ሀዋሳን ከፍፁም የጨዋታ የበላይነት ጋር በጎል አንበሽብሾ የተጠናቀቀ ነበር፡፡ በሁሉም ረገድ ተሽለው የቀረቡት እንስት ኃይቆቹ ገና በጊዜ 5ኛው ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ ባስቆጠረችው ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡ መነሻውን ከአማካዩዋ ሲሳይ ገብረዋህድ እግር ስር ካደረጉ ኳሶች በፈጣን ሽግግር ጥቃትን መሰንዘራቸውን ያጠናከሩት ሀዋሳዎች ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ቱሪስት ለማ በግል ጥረቷ የተገኘን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጣው የቡድኗን የጎል መጠን ከፍ አድርጋለች፡፡ 34ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ቱሪስት ለቡድኗ እና ለራሷ ሀት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል አክላ ወደ መልበሻ ክፍል ጨዋታው አምርቷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው አሁንም የሀዋሳ አይምሬነት በድጋሚ ጎልቶ እንዲታይ ያስቻለ ሆኗል፡፡ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ቱሪስት በዚህኛውም አጋማሽ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ያገኘችውን ኳስ ስልነቷን በደንብ ያሳየን ጎል ከመረብ አዋህዳ ውጤቱም 4-0 አድርሳለች፡፡ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ደርሶ ጎል ለማስቆጠር ተከላካዮችን አልፎ ጎልን ለማግኘት የተቸገሩት ንፋስ ስልኮች በአንፃሩ አምስተኛ ጎል በረድኤት አስረሳኸኝ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎችም ታሪኬ ጴጥሮስ ፣ ሳራ ነብሶ እና ረድኤት አስረሳኸኝ ተጨማሪ ጎልን አክላ ጨዋታው በሀዋሳ 8-0 የበላይነት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለሀዋሳ አራት ግቦችን ያስቆጠረችው ቱሪስት ለማ የጨዋታ ምርጥ በመባል ተመርጣለች፡፡

የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ በነበረው የይርጋጨፌ ቡና እና ልደታ ክፍለከተማ መርሀግብር አንድም የተለየ የሜዳ ላይ ልዩነትን ሳንመለከት አሰልቺ እንደነበር ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡ የልደታ ክፍለከተማዋ ተጫዋች መሰረት ምክሬ የዚህ ጨዋታ ምርጥ በመባል ተሸልማለች፡፡

ያጋሩ