ያለፉትን ሳምንታት በኃይቆቹ ቤት መነጋገሪያ የነበረው የወንድማገኝ ኃይሉ ጉዳይ መቋጫ ማግኘቱ ታውቋል።
ሀዋሳ ከተማ እና ተጫዋች ወንድማገኝ ኃይሉ ከውል ስምምነት ጋር በተያያዘ አለመግባባት ውስጥ ገብተው እንደነበረ አይዘነጋም። ሀዋሳ ከተማ ወንድማገኝ ከ2013 እስከ 2016 ጥቅምት 30 ቀን ድረስ ለሦስት ዓመት የሚያቆየው የውል ስምምነት እንዳለው ሲገልፅ ተጫዋቹ በበኩሉ የውል ዘመኔ የሚጠናቀቀው በ2015 ጥቅምት 30 ነው በማለት የሰነድ ማስረጃ በመያዝ ጉዳያቸው ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማምራቱንም መዘገባችን ይታወቃል። በዚህም መነሻነት ተጫዋቹ ሀዋሳ ከተማ በድሬደዋ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ላይ ግልጋሎት ሳይሰጥ ቆይቷል።
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘቸው መረጃ መሠረት በወንድማገኝም ኃይሉ እና በክለቡ መካከል የተፈጠረው አለመግባበት በንግግር እንደተፈታ እና ተጫዋቹ በአሳዳጊው ክለብ እንደሚቆይ ለፌዴሬሽኑ ማረጋገጫ መስጠቱ ተረጋግጧል። በዚህም መሠረት ተጫዋቹ የፊታችን ሰኞ ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ጋር በሚያደርገው የአስረኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ቡድኑን ማገልገል እንደሚቀጥል ይጠበቃል።