ሪፖርት | የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታም በአቻ ውጤት ተደምድሟል

በኢትዮጵያ መድን እና ሀዋሳ ከተማ መካከል የተደረገው ፍልምያ ያለ ግብ ተጠናቋል።

በ9ኛ የጨዋታ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ 3-1 የተረቱት ኢትዮጵያ መድኖች አንድም ተጫዋች ሳይቀይሩ ወደ ሜዳ ሲገቡ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት ለምንም የተሸነፉት ሀዋሳዎች በበኩላቸው በብርሃኑ አሻሞ፣ ሙጂብ ቃሲም ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ እና እዮብ አለማየሁ ምትክ በቃሉ ገነነ ፣ ተባረክ ሄፋሞ ፣ ዓሊ ሱሌይማን እና ሰለሞን ወዴሳ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጨዋታው በተጀመረ ገና በ53ኛው ሰከንድ በረጅሙ የተላከን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ የነበረው ኪቲካ ጅማ ሞክሮት ኢትዮጵያ መድኖች በጊዜ መሪ ሊሆኑ ነበር። በ5ኛው ደቂቃም አብዱልከሪም መሐመድ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሲሞን ፒተር እንዳገኘው መትቶት የወጣው አጋጣሚ በድጋሚ በመድኖች በኩል የታየ ጥቃት ነው። ኳሱን ለመድኖች ሰጥተው መንቀሳቀስ የመረጡት ሀዋሳዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ መድሃኔ ብርሃኔ ከግራ መስመር አሻምቶት ተባረክ እና ዓሊ ተባብረው ሞክረውት የግቡ ቋሚ በመለሰው ኳስ የመጀመሪያ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል።

የሀዋሳን ግብ መጎብኘት አጠናክረው የቀጠሉት መድኖች በ22 እና 24ኛው ደቂቃ ተከታታይ የተሻሉ ዕድሎችን በአጥቂያቸው ሲሞን ፒተር አማካኝነት ፈጥረው ተመልሰዋል። በተለይ በሁለተኛው አጋጣሚ ተጫዋቹ ተከላካዮችን አልፎ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ የመታው ኳስ የግቡ አግዳሚ በአስቆጪ ሁኔታ ከግብነት ታድጎታል። ቀስ እያሉ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ለማድረግ መጣር የጀመሩት ሀዋሳዎች በ29ኛው ደቂቃ በቃሉ ገነነ እንዲሁም በ31ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደርቤ በሞከሯቸው ኳሶች ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራን ፈትነው ነበር። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጨዋታው የግብ ሙከራዎችን ባያስተናግድም ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር አስመልክቷል።

ሁለተኛውን አጋማሽም በፈጣን ሁኔታ የጀመሩት መድኖች በቀኝ መስመር በኩል ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል አምርተው በባሲሩ ዑመር አማካኝነት ሙከራ አድርገው የነበረ ቢሆንም መሐመድ ሙንታሪ ዕድሉም አምክኖባቸዋል። በ55ኛው ደቂቃም ከተመሳሳይ መስመር የተነሳን ኳስ ተከላካዩ ሰለሞን በሚገባ ማፅዳት ሳይችል ቀርቶ ኪቲካ አግኝቶት የግብ ምንጭ ሊያደርገው ነበር።

በአጋማሹ ጅማሮ ጫና የበዛባቸው ሀዋሳዎች ፈጣኖቹን አጥቂዎቻቸው ለመጠቀም ተደጋጋሚ ሽግግሮችን መጠቀም ያዘወተሩ ሲሆን በ60ኛ ደቂቃ መባቻ ላይም ዒሊ ባመከነው ኳስ አስቆጪ ዕድል ፈጥረው ተመልሰዋል። በ69ኛው ደቂቃ መገባደጃ ግን ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። በዚህም 68ኛው ደቂቃ ላይ ፒተር በ69ኛው ደቂቃ ደግሞ ተቀይሮ የገባው ሀቢብ ከሳጥን ውጪ በቀኝ እና በግራ እግራቸው በሞከሯቸው ኳስ ጥሩ ዒላማውን የጠበቀ ጥቃት ተሰንዝሮባቸው የግብ ዘባቸው ዕድሎቹን አምክኗቸዋል።

በ81ኛው ደቂቃ ደግሞ ከ180 ሰከንዶች በፊት ኪቲካን ቀይሮ የገባው ያሬድ ዳርዛ የተተፋን ኳስ በመጠቀም ሌላ ጥቃት ሰንዝሮ መክኖበታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዊች ሲቀሩት የጨዋታው የመጨረሻ የግብ የቀረበ ዕድል ተስተናግዶ በግብ ጠባቂ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። በዚህም ያሬድ በድጋሚ ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ መትቶ ሙንታሪ በጥሩ ቅልጥፍና መልሶታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ያጋሩ