መረጃዎች | 37ኛ የጨዋታ ቀን

በሊጉ 10ኛ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አሰናድተናል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

የዕለቱ የመጀመሪያ በሆነው መርሐግብር እኩል 14 ነጥቦች ላይ የሚገኙት እና ጥሩ የሆነ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙትን ድሬዳዋ ከተማዎችን ከወልቂጤ ከተማ ያገናኛል።

በከተማቸው አልቀመስ ያሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በሰንጠረዡ ሽቅብ መጓዛቸውን ቀጥለው አሁን ላይ በ14 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ከኳስ ውጭ አመዛኙን ደቂቃ የሚያሳልፈው ቡድኑ ቢኒያም ጌታቸውን ዒላማ ባደረጉ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ሲጥር ዩጋንዳዊው ቻርልስ ሙሴጌ ከቀደሙት ጨዋታዎች በተሻለ ይበልጥ ወደ መሀል ለቢኒያም ቀርቦ እንዲጫወት መደረጉ እንዲሁ ምቾት የሰጠው ይመስላል። ሙሴጌም ከኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ አንስቶ ባደረጋቸው ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ እያስቆጠረ ይገኛል።

ከፍ ባለ ፍላጎት ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች በሜዳቸው ያላቸው የማሸነፍ ግስጋሴ ለማስቀጠል በነገውም ጨዋታ በተሻለ መነሳሳት እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።

በሊጉ ጥሩ አጀማመር ካደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ነጥብ ተጋርተው የተመለሱት ወልቂጤ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ጋር እኩል 14 ነጥብ ቢኖራቸውም በግብ ክፍያ ተበልጠው በአንድ ደረጃ ዝቅ ብለው 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ኳስን ለመቆጣጠር ታልሞ የተገነባ የሚመስለው ስብስብ ባለፉት ጨዋታዎች ግን ከሜዳው ሁኔታ አስገዳጅነት ጋር በተያያዘ ምክንያት ይበልጥ በቀጥተኛ መንገድ እየተጫወቱ ቢገኙም ውጤታማ ግን ለመሆን እየተቸገሩ ያሉ ይመስላል በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ ቡድን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ፍፁም ተቸግሮ ተመልክተናል። በነገው ጨዋታ ተጋጣሚያቸውም ይበልጥ በረጃጅም ኳሶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ለመዱት የኳስ ቁጥጥር ሊመለሱ እንደሚችል ሲገመት ቡድኑ ውጤትን ይዞ ለመውጣት የጌታነህ ከበደን ብቃት ይፈልጋል።

በኢንተናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው መሪነት በሚጀምረው ጨዋታ በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ከተከላካዩ ቴዎድሮስ ሀሙ ውጪ የተቀሩት ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ሙዲኽን ሙሳ እና አቤል ከበደ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በክለቡ በዲሲፕሊን ጥሰት ምክንያት ቅጣት ላይ የሚገኘው ፍሬው ጌታሁን እና እንየው ካሳሁንም እንዲሁ ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ሲገናኙ ወልቂጤ ከተማ ሁለት ጊዜ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ አንዴ አሸንፈው በመጨረሻ ጨዋታቸው ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ወልቂጤ ስድስት ድሬዳዋ ደግሞ አራት ግቤችን አስቆጥረዋል።

ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

ዘንድሮ በወትሮው የዋንጫ ፉክክር ደረጃ ውስጥ ለመገኘት የተቸገሩት ሲዳማ እና ፋሲል በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት የሚፈልጉትን ድል ማሳካት ከቻሉ በኋላ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። ሁለቱ ቡድኖች በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ተለያይተው በሚያደርጉት ጨዋታ ማሸነፍ የቻለው ቡድን በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ ለመቀመጥ ይችላል።

የነገውን ጨዋታ ከሲዳማ ቡና አንፃር ስንመለከተው አሰልጣኝ ስዩም ከበደን ማንሳት የግድ ይላል። ካቻአምና የሊጉን ክብር ካሳኩበት የቀድሞው ክለባቸው ጋር መገናኘታቸው ከሚሰጠው ትኩረት ባለፈ በቅርብ ጊዜያት ያሰለጠኗቸውን ተጫዋቾች በተቃራኒ መግጠማቸው ለጨዋታ ዕቅዳቸው እንደሚረዳቸው መገመት አያዳግትም። ሲዳማ ከመድኑ ሽንፈት ማግስት በመቻሉ ጨዋታ የሰጠው ምላሽ ፋሲልን ከመግጠሙ በፊት ጥሩ መንፈስ ላይ እንዲገኝ የሚረዳው ነጥብ ነው። በርካታ የተጫዋቾች ለውጥ ባደረገበት ጨዋታ የተጋጣሚን እንቅስቃሴ በማፈን እና ጥቃት በመሰንዘሩ ረገድ ያሳየው ስኬትም ለነገ የጨዋታ ዕቅዱ የሚተርፍ ይመስላል።

ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ መሉ ነጥብ ማሳካት ለቻለው ፋሲል ከነማ ለገጣፎ ላይ ያሳካው ድል ዋጋ ትልቅ ነው። ቡድኑ ይህንኑም ጨዋታ የጀመረበት አኳኋን ጥሩ ያልነበረ ቢሆንም በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ባደረጋቸው ለውጦች ብልጫ የወሰደበት መንገድ በነገ አቀራረቡ ላይ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። በተለይም ተቀይረው የገቡት ሱራፌል ዳኛቸው እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እንቅስቃሴ በሲዳማው ጨዋታ ቀዳሚ አሰላለፍ ላይ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚጠቁም ነበር። በጥቅሉ ቡድኑ ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዛ ከነበረበት ጫና አንፃር መረቡን ሳያስደፍር ወደ አሸናፉነት መምጣቱ ከነገው ዓይነት ጠንከር ያለ ፍልሚያ በፊት የሚኖረውን የሥነ ልቦና ደረጃ ከፍ የሚያደርግለት እንደሆነ ይታመናል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በሚመሩት በዚህ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ሰላዲን ሰዒድ እና ሙሉቀን አዲሱን በጉዳት መክብብ ደገፉን በቅጣት የሚያጣ ሲሆን በፋሲል ከነማ በኩል ሀብታሙ ተከስተ ብቻ ከጨዋታው ውጪ እንደሆነ ነው።

ሁለቱ ቡስኖች በሊጉ ከተገናኙባቸው አስር ጨዋታዎች ውስጥ ነጥብ በመጋራት የተጠናቀቀ ጨዋታ የሌለ ሲሆን 15 ግቦች ያስቆጠረው ፋሲል ከነማ ስድስት እንዲሁም 11 ግቦች ያስመዘገበው ሲዳማ ቡና ደግሞ አራት ጊዜ ድል አድርገዋል።