አማኑኤል ዩሐንስ ቀጣይ ጨዋታዎች ያመልጡታል

የኢትዮጵያ ቡናው አንበል አማኑኤል ዩሐንስ በተወሰኑ ጨዋታዎች ለቡድኑ ግልጋሎት እንደማይሰጥ ታውቋል።

ከተስፋ ቡድን አንስቶ ያለፉትን ስድስት ዓመታት እያገለገለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ አማኑኤል ዩሐንስ ጉዳት አጋጥሞታል። ኢትዮጵያ ቡና በስምንተኛው ሳምንት ከባህርዳር ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የብሽሽት ጉዳት ያስተናገደው አማኑኤል ዮሐንስ በ24ኛው ደቆቃ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዶ እንደነበር አይዘነጋም። ቀጣዩ የዘጠነኛው ሳምንት ጨዋታ ያመለጠው አማኑኤል ከነገው የለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታ ውጭ መሆኑም ታውቋል።

ተጫዋቹ በክለቡ ፊዞትራፒስት ይስሐቅ ሽፈራው የህክምና ክትትል እየተደረገለት እንደሆነ እና ለቀጣይ ጨዋታ ዝግጁ መሆን አለመሆኑ እንደሚታወቅ ሰምተናል። ይህም ቢሆን አማኑኤል በ11ኛ ሳምንት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የሚኖረው ጨዋታም ሊያመልጠው እንደሚችል ተገምቷል።

ያጋሩ