ሪፖርት | ብርትካናማዎቹ እና ሠራተኞቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ሳቢ የሜዳ ላይ ፉክክር ያስመለከተው የድሬዳዋ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ሁለት አቻ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን ሦስት ለአንድ የረታው ድሬዳዋ ከተማም ሆነ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው ወልቂጤ ከተማ በአሰላለፋቸው ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጨዋታውን በጥሩ ተነሳሽነት የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች ገና ሁለት ደቂቃ ሳይሞላ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። በዚህም በረጅሙ የተመታን ኳስ የተከላካይ አማካዩ ዮሴፍ ዮሐንስ በግንባር ወደ ኋላ አቀብላለው ብሎ ለጌታነህ የሰጠውን ኳስ አጥቂው ተከላካዮችን በማታለል በግራ እግሩ ግብ አድርጎታል። 

በጊዜ በተቆጠረው ጎል የተደናገጡ የሚመስሉት ድሬዎች በኋላ መስመራቸው ላይ ተደጋጋሚ የቅብብል ስህተቶችን ቢፈጥሩም ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚታወቁበትን ረጃጅም ኳሶች ማዘውተር ይዘዋል።

12ኛው ደቂቃ ላይም ኤሊያስ አህመድ በተከላካዮች መካከል የላከውን ተንጠልጣይ ኳስ ቢኒያም ጌታቸው ፈጥኖ ቢያገኘውም ከመጠቀሙ በፊት ተስፋዬ መላኩ ደርሶ መልሶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ይኸው አጥቂ በተመሳሳይ አጨዋወት የቡድኑን የአቻነት ግብ አስቆጥሯል። በዚህም በረጅሙ የተላከን ኳስ ቀድሞ የቢኒያምን ዕድል ያጨናገፈው ተስፋዬ በሚገባ ማፅዳት ተስኖት ሲጨርፈው ቢኒያም ደርሶበት የተስፋዬን ስህተት ለማረም ክልሉን ለቆ የወጣው ግብ ጠባቂ ፋሪስ አናት ልኮት ግብ ተቆጥሯል።

ገና በሩብ ሰዓት ሁለት ጎል ያስተናገደው ጨዋታው ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ማስመልከቱን ቀጥሎበታል። በ28ኛው ደቂቃም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጌታነህ ወደ ቀኝ ካደላ ቦታ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ያዳነበት ዕድል የተመልካችን ቀልብ የገዛ ጥቃት ነበር። በ30ኛው ደቂቃ ደግሞ ድሬዳዋ ለተሰነዘረበት ጥቃት አፀፋዊ ምላሽ ሰጥቶ ተመልሷል። በዚህ ደቂቃም ተስፋዬ በድፋሜ የራሱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ሆኖ በወረደ የውሳኔ አሰጣጥ የተቀማውን ኳስ ቢኒያም ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ሊያደርገው ቢሞክርም የግብ ዘቡ ፋሪስ በቅርቡ ቋሚ የተመታውን ኳስ ከግብነት ታድጓታል።

ፍልሚያው ተጋግሎ ሲቀጥል በ38ኛው ደቂቃ ሦስተኛ ግብ ተስተናግዶበታል። ከግራ መስመር የተሻማን ኳስ አቡበከር ሳኒ ለመጠቀም ሲጥር መሐመድ አብዱለጢፍ ጥፋት ሰርቶበት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም ጌታነህ ከበደ ቡድኑን ዳግም መሪ እንዲሆን አስችሎበታል። አምበሉ ጌታነህ በ44ኛው ደቂቃም ከመዓዘን ምት ቀጥታ መትቶ ግብ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በግብ ጠባቂው ባይመክን ኖሮ ወልቂጤ ሦስት ለአንድ እየመራ ወደ እረፍት ያመራ ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ የኋላ መስመራቸው ላይ ስህተቶችን ሲሰሩ የነበሩት ድሬዳዋዎች በ33 እና በአጋማሹ የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ውቅራቸውን ለማሻሻል የሞከሩ ሲሆን የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችንም በማስገባት ጨዋታውን ማሳደድ ቀጥለዋል። አጋማሹ በተጀመረ በ10ኛው ደቂቃም መሐመድ አብዱለጢፍ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ቢኒያም ቀኝ እግሩን ሰንዝሮ ለማግኘት ጥሮ ሳይሳካለት በቀረው ኳስ አቻ ሊሆኑ ነበር። በ67ኛው ደቂቃ ደግሞ ኤሊያስ አህመድ ከሳጥን ውጪ ጥብቅ ኳስ ልኮ ዒላማውን ስቶበታል።

ወልቂጤዎች በበኩላቸው እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተጭነው የድሬን ስህተት እያነፈነፉ መጫወታቸውን ቢቀንሱም የሚገኙ ዕድሎችን በረጅሙ በመላክ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተንቀሳቅሰዋል። በተለይ ጌታነህን ዒላማ ያደረጉ ኳሶች በተደጋጋሚ ሲልኩም ተስተውሏል። ነገር ግን ይህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደ መጀመሪያው ብዙ ሙከራዎች የነበሩበት አልነበረም።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት በመቀመጫ ከተማቸው እየተጫወቱ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች የአቻነት ግብ አግኝገዋል። በዚህም ከመዓዘን ምት አብዱለጢፍ መሐመድ ያሻማውን ኳስ እያሱ ለገሰ በግንባሩ ግብ አድርጎት ድሬ አቻ ሆኗል። ጨዋታውም ሁለት አቻ ተጠናቋል።