የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ3ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ሀዋሳ ከተማ መሪነቱን የሚያጠናክርበት ነጥብ ሲጥል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አርባምንጭ ከተማ በበኩላቸው ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ወሳኝ ድል አሳክተዋል፡፡
በሀዋሳ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ዛሬ በ3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጅምሩን አድርጓል፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል ቀዳሚ የነበረው የሳምንቱ ጨዋታ ቅድሚያውን ይወስዳል፡፡ በተያዘለት 4 ሰዓት ላይ ይሄ ጨዋታ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም የአንደኛ ሊግ የመክፈቻ ጨዋታን የሀዋሳው አርቴፊሻል ሜዳ የሚያስተናግድ በመሆኑ ምክንያት የሰዓት ማሻሻያ ተደርጎበት ጨዋታው ማለዳ 2 ሰዓት ላይ ተከናውኖ ነጥብ በመጋራት ተጠናቋል፡፡
ተመጣጣኝ የጨዋታ ቅርፅ በነበረው እና ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን ይህ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የጠሩ አጋጣሚዎችን ያስመለከተን ከዕረፍት በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች ላይ ነበር፡፡ አጋማሹ ከተጀመረ ሰባት ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ቱሪስት ለማ የደረሳትን ኳስን ወደ ጎልነት ለውጣው ክለቧን መሪ ያደረገች ሲሆን በግሏም የኮከብ ግብ አግቢነቱን ወደ አምስት አሳድጋለች፡፡ ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በይበልጥ ነቅለው ወደ ማጥቃት ሽግግሩ ፊታቸውን በደንብ ያተኮሩት ልደታ ክፍለከተማዎች አምበሏ አለሚቱ ድሪባ ከርቀት አክርራ ወደ ጎል ስትመታ በሀዋሳዋ ተከላካይ ማዕደር ባዬ ተጨርፎ ከመረብ ያረፈችው ኳስ ልደታ አቻ በማድረግ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ የልደታ ክፍለከተማዋ አማካይ ህዳት ካሱ የጨዋታው ኮከብ ተብላ ተሸልማለች፡፡
የዕለቱ ሁለተኛ መርሀ ግብር የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቦሌ ክፍለከተማ ጨዋታ ንግድ ባንክን በጎል አንበሽብሾ ባለ ድል አድርጎ የተጠናቀቀ ነበር፡፡
በመጀመሪያው የጨዋታው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ ብልጫን ወስደው የተንቀሳቀሱት ንግድ ባንኮች የሚያገኙትን ኳስ ተቀባብሎ ወደ ሳጥን ከመድረስ ይልቅ በረጃጅሙ ከሚጣሉ ኳሶች መነሻቸውን አድርገው ለመጫወት ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፡፡ ገና በጊዜ በአረጋሽ እና የምስራች አማካኝነት ፈጣን ጥቃትን መሰንዘር የጀመሩት ንግድ ባንኮች 4ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ ባስቆጠረችው ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡ የቦሌ ተጫዋቾች ኳስን ተቀባብሎ በመጫወት ከራሳቸው የግብ ክልል አልፎ ለማጥቃት ይቸገሩ የነበሩ ሲሆን በዚህም ድክመታቸው ሁለተኛ ጎልን ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ አረጋሽ ካልሳ አስቆጥራባቸዋለች፡፡
አምበሏ ሎዛ አበራ 16ኛው ደቂቃ ላይ የምስራች ላቀው የግል ጥረቷን ተጠቅማ የሰጠቻትን ኳስ በማስቆጠር የባንክን የጎል መጠን ከፍ ማድረግ ችላለች፡፡ ከተሻጋሪ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ከጎል ጋር ሲገናኙ የነበሩት የአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ልጆች 41ኛው ደቂቃ የምስራች ላቀው አራተኛ ጎል ስታስቆጥር አረጋሽ ካልሳ በመጀመሪያው አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ አምስተኛ ጎልን አክላለች፡፡ ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ንግድ ባንኮች ከቀዳሚው የጨዋታ አጋማሽ አንፃራዊ መቀዛቀዞች የታየባቸው ሲሆን በአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ የሚመራው ቦሌ ክፍለከተማ በአንፃሩ እጅጉን ተሻሽለው ብርቱ የሜዳ ላይ ፉክክርን ማሳየት ቢችሉም በመጀመሪያው አጋማሽ የተቆጠሩባቸው አምስት ግቦች ንግድ ባንክን በጎል ታጅቦ 5-0 አሸናፊ መሆን እንዲችል አድርጓል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሁለት ጎሎችን አስቆጣሪዋ አረጋሽ ካልሳ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡
10 ሰዓት ሲል አርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማን ያገናኘው ጨዋታው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ነበር፡፡ እጅግ አስገራሚ የሜዳ ላይ ትግልን ባየንበት በዚህ ጨዋታ የአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልዱ አርባምንጭ ተጫዋቾች ያገኙትን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ሙሉ ነጥብን ሸምተዋል፡፡
የተከላካይ ስፍራ ተሰላፊዋ ከአምላክነሽ ሀቁ ከሳጥን ውጪ ከመረብ ባሳረፈችው ግብ አርባምንጮች መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ኳስን በመነካካት በሂደት ወደ አርባምንጭ ከተማ የግብ ክልል ሲደርሱ የስልነት ችግሮች የሚታይባቸው አዲስ አበባ ከተማዎች ከዕረፍት በኋላ 82ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ድንቅ ግብ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ አጥቂዋ ቤተልሔም ሰማን ከሳጥን ውጪ እጅግ ድንቅ ግብን የቀድሞው ቡድኗ ላይ አክላ ጨዋታው በእንስት አዞዎቹ 2-0 አሸናፊነት ፍፃሜን አግኝቷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የአርባምንጯ ተከላካይ ድርሻዬ መንዛ የጨዋታው ምርጥ በመባል ተሸልማለች፡፡