በአስረኛ የጨዋታ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ

የዕለቱ የመጀመሪያ መርሃግብር ከድል የታረቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶችን በተከታታይ አውንታዊ ውጤቶችን መሰብሰብ ከጀመሩት ወላይታ ድቻዎች ያገናኛል።

ከተከታታይ አራት ጨዋታዎች በኃላ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በመርታት ወደ ድል የተመለሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነጥባቸውን ወደ 18 በማሳደግ አሁን ላይ በሰንጠረዡ በ2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በሀዋሳው ጨዋታ ቡድኑ እንደቀደመው ጊዜ ከጨዋታው ጅማሬ አንስቶ ጫና በመፍጠር መልካም የሚባል አጀማመርን ለማድረግ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በዚህም በመጀመሪያዎቹ 32 ደቂቃዎች ሦስት ግቦችን ማግኘት አስችሏቸዋል። ምንም እንኳን ሀዋሳ ከተማዎች በርከት ያሉ ደቂቃዎችን በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ቢገደዱም ፈረሰኞቹ ግን ያንን ተነሳሽነት ማስቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል።

በመጨረሻው ጨዋታ በተለይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በቀኝ መስመር ፣ ቢኒያም በላይ በመሀል አማካይነት እንዲሁም ጋቶች ፖኖም በተከላካይ አማካይነት ሚና የነበራቸው አበርክቶ እጅግ አስደናቂ የነበሩ ሲሆን የአምና የሊጉ አሸናፊዎች ነገም ተጋጣሚያቸውን ለማሸነፍ የሦስቱን ተጫዋቾች ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሆነ ፈጠን ያለ አጀማመር ስለማድረግ ያልማሉ።በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት አዲስ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ የነበሩት ዳዊት ተፈራ ፣ ሻሂዱ ሙስጠፋ እና ተመስገን ዮሀንስ በተመሳሳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ እጅግ አሰልቺ በነበረው ጨዋታ ነጥብ ተጋርተው የወጡት ወላይታ ድቻዎች በ9 ነጥቦች በሰንጠረዡ በ11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ላለመሸነፍ ቅድሚያ የሰጠ በሚመስል አቀራረብ ወደ ግብ ክልላቸው ቀርበው ለመከላከል እና ከተቻለም በረጃጅም ከሚጣሉ ኳሶች የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ኳሶችን በማሸነፍ ለመጫወት ቢሞክሩም ጥረታቸው እምብዛም የሰመረ አልነበረም። በነገው ጨዋታ ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ መሆኑን ተከትሎ ከአርባምንጩ ጨዋታ በበለጥ ለጥንቃቄ ቅድሚያ ይሰጣሉ ተብሎ ይገመታል።በወላይታ ድቻዎች በኩል እንድሪስ ሰዒድ እና መሳይ ኒኮል በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን በባለፈው ጨዋታ ያልነበረው ንጋቱ ገ/ስላሴ ግን መሻሻሎችን ቢያሳይም በነገው ጨዋታ በመጀመሪያ ተሰላፊነት መጀመሩ ግን አጠራጣሪ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 16 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ፈረሰኞቹ 7 ጊዜ እንዲሁም የጦና ንቦቹ ደግሞ 5 ጊዜ (አንድ ፎርፌን ጨምሮ) ድል ማድረግ ሲችሉ የቀሩት 4 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።ይህን 10 ሰዓት ሲል ጅማሮ የሚያደርገውን የሁለቱን ቡድኖቾ ጨዋታ አባይነህ ሙላት በመሀል ዳኝነት ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ባህር ዳር ከተማ

የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር መጠነኛ መቀዛቀዝ ላይ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎችን ከወቅቱ የሊጉ ምርጥ ቡድን ባህር ዳር ከተማ ጋር ያገናኛል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጥሩ ከነበረው የውድድር ዘመን ጅማሯቸው ማግስት በተወሰነ መልኩ እየተቀዛቀዙ ያሉ ይመስላል።በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ የጣለው ቡድኑ
በ15 ነጥቦች በሰንጠረዡ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በተለይ ወልቂጤን በገጠሙበት ጨዋታ የነበራቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ፍፁም ተዳክሞ ተመልክተናል።ፊት ላይ እና መሀል ክፍሉ ላይ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በጉዳት ያጣው ቡድን በዚህ መነሻነት ቡድኑ በተወሰነ መልኩ ከቀደመው ቅኝቱ የወጣ ይመስላል።በተለይ በሽግግሮች ለማጥቃት የሚፈልገው ቡድኑ ይህን ለማድረግ እየተቸገረ የሚገኘው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ግርማ በቀለ በቅጣት እንዲሁም መለሰ ሚሻሞ እና ቤዛ መድህን በጉዳት የማያገኙ ሲሆን እንዳለ ደባልቄ ግን ከጉዳት የሚመለስ ይሆናል።

በሊጉ በወቅታዊ ብቃት እጅግ ምርጥ ቡድን የሆነው ባህር ዳር ከተማ ድሬዳዋ ላይ ባስመዘገቧቸው ሦስት ተከታታይ ድሎች መነሻነት በ17 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ከጨዋታ ጨዋታ ይበልጥ እየተዋሀደ እና እየጎለበተ የሚገኘው ቡድኑ በተለይም ከወገብ በላይ የሚገኙት ተጫዋቾች ከፊት አጥቂ ስፍራ ውጭ ምርጥ ብቃታቸው ላይ መገኘታቸው ቡድኑን ይበልጥ አስፈሪነት እያላበሱት ይገኛሉ።ድንቅ የሆነ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ፉዓድ ፈረጃ የቡድኑ ማጥቃት በመዘወር ረገድ እጅግ ወሳኙ ተጫዋች ነው በተለይ የመስመር ተጫዋቾቹን እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ ከተከላካይ ጀርባ የሚጥላቸው ጊዜያቸውን የጠበቁ ኳሶች በመስመር ተጫዋቾቹ ማጥቃትን ምርጫው ላደረገው ቡድኑ እጅግ ወሳኝ ናቸው።

በመከላከሉ ረገድ ይበልጥ ሚዛናዊ እየሆነ የመጣው ቡድኑ ከተወሰኑ ግለሰባዊ ስህተቶች ውጭ መከላከሉም እንደ ማጥቃቱ ይበልጥ እየተሻሻለ ይገኛል።አሰልጣኝ ደግዓረግ ይግዛው አጥቂውን ፋሲል አስማማውን በነገው ጨዋታ በጉዳት የሚያጡት ሲሆን በአዳማው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ፉዓድ ፈረጃ ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።

በሀዲያ ሆሳዕናዎች በኩል ምንም እንኳን እንደ ባህር ዳር በትልቁ የሚነሳ ባይሆንም ብርሃኑ በቀለ የሚጫወትበት የቡድን የቀኝ ወገን ጥሩ የሚባል ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ የነገው ጨዋታ በመስመሮች ላይ በሚኖር እንቅስቃሴ የሚወሰን ሊሆን ይችላል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ሁለት ሁለት ጊዜ መሸናነፍ ችለዋል።የምሽቱን ጨዋታ ሄኖክ አክሊሉ በመሀል ዳኝነት እንደሚመሩት ይጠበቃል

ያጋሩ