ባህር ዳር ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን ሁለት ለምንም በመርታት ሁለተኛ ደረጃን ተረክቧል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ከተለያየበት የ9ኛ ሳምንት ፍልሚያ ስቴቨን ኒያርኮ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎን በፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን እና ባዬ ገዛኸኝ ለውጦ ወደ ሜዳ ሲገባ አዳማን አንድ ለምንም ረትቶ ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጀው ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ የራቀው ፋሲል አስማማውን ብቻ በሀብታሙ ታደሠ ለውጦ ጨዋታውን ጀምሯል።
ጥሩ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በ6ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት አስተናግዶ የተመልካቾችን ቀልብ ገዝቷል። በዚህም ሀዲያዎች ያሬድ ባየ በራሱ ሳጥን ጥፋት ሰርቶ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በመጠቀም ቀዳሚ ይሆናሉ ተብሎ ቢጠበቅም ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን የመታውን ኳስ የግብ ዘቡ ፋሲል ገ/ሚካኤል አድኖታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ጨዋታው የመጀመሪያ ግብ ተቆጥሮበታል። በዚህም በፍፁም ቅጣት ምቱ ሳይደናገጡ ጨዋታውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች በ10ኛው ደቂቃ መሪ ሆነዋል። የግራ መስመር ተከላካዩ ሔኖክ ያሻማውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶን በማታለል ግብ አድርጎታል።
ከሳጥን ሳጥን የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ማስመልከት የቀጠለው ጨዋታው በ23ኛው ደቂቃ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ በሀዲያዎች በኩል ተፈጥሮበታል። በዚህም የፍፁም ቅጣት ምቱን ሳይጠቀምበት የቀረው ፍቅረየሱስ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በሩቁ ቋሚ የነበረው ራምኬል ሎክ ተቆጣጥሮት ቢሞክረውም ዕድሉ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ግብ ጠባቂ ፋሲል ተመልሷል። ወደ ጎል ሲያመሩ አስፈሪ የሆኑት ባህር ዳሮች በ32ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን አሳድገዋል። በዚህም ፉዐድ ፈረጃ ወደ ቀኝ ካደላ ቦታ ዳግም ንጉሴ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ መሬት ለመሬት በመምታት ሰይዶ መረብ ላይ አሳርፎታል።
ባህር ዳር መሪነቱን ካሳደገ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ለሦስተኛ ግብ ተቃርቦ ነበር። ተከላካዮችን አፈትልከው በመውጣት የተገኘን አጋጣሚ ሀብታሙ ታደሰ የራስ ወዳድነት ስሜት ሳያሳይ ለፉዐድ ቢያቀብለውም ፉዐድ ግብ ጠባቂው ታልፎ የደረሰውን ኳስ በወረደ ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በቀጣዮቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ሀዲያዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩበት ሆኗል። በቅድሚያ በ38ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ብርሃኑ ከሳጥን ውጪ ሲሞክር በቀጣይ ደግሞ በ44ኛው ደቂቃ ባዬ ከቅጣት ምት ኳስ ወደ ግብ ልኮ ግብ ጠባቂው ፋሲል አምክኗቸዋል።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቀዝቀዝ ያለው ጨዋታው እምብዛም የግብ ሙከራዎች የበረከቱበት አልነበረም። በአንፃራዊነት ተመሪዎቹ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጨዋታውን በማሳደድ አንዳች ነገር ለማግኘት የተሻለ ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበረ ሲሆን ከወገብ በላይ ያሉ ተጫዋቾችንም በመቀየር የማጥቃት ኃይላቸውን ለማደስ ጥረዋል። ባህር ዳሮች በበኩላቸው በእጃቸው የገባውን ውጤት ለማስጠበቅ ጨዋታ ቁጥጥር ላይ ትኩረት ሰጥተው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በዚህኛው አጋማሽም የመጀመሪያ የሰላ ጥቃት የተሰነዘረው በ71ኛው ደቂቃ ነው። በዚህም ሀብታሙ በቀኝ መስመር የደረሰው ኳስ አክርሮ በመምታት ለግብ ምንጭነት ቢጠቀመውም ዒላማውን ስቶበታል።
ሀዲያዎች በ81ኛው ደቂቃ ማስተዛዘኛ የሚሆን ጎል ለማግኘት እጅግ ተቃርበው የነበረ ቢሆንም በጨዋታው እጅግ ምርጥ ብቃት ያሳየው ግብ ጠባቂው ፋሲል በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል። በቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ሙከራ ሳይደረግ ፍልሚያው በባህር ዳር ከተማ ሁለት ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።