የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሦስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ሲጠናቀቁ መቻል ፣ ይርጋጨፌ ቡና እና አዳማ ከተማ ወሳኝ ሙሉ ነጥብ ያገኙበትን ድል አሳክተዋል፡፡
መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ረፋድ 4 ሰዓት ሲል ጀምሯል፡፡ ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከዕረፍት በፊት ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወቱ ረገድ ተመጣጣኝነት ያለውን እንቅሴቃሴን መመልከት ብንችልም ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ደርሶ ጎል በማስቆጠሩ የአሰልጣኝ ስለሺ ገመቹው መቻል በአንፃራዊነት እጅጉን የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡
14ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ሳራ ኪዶ እና ማዕድን ሳዕሉ በመጨረሻም የሰጧትን ኳስ ከግራ አቅጣጫ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት እፀገነት ግርማ ወደ ጎል አክርራ ስትመታው የግብ ጠባቂዋ ብርሀን ባልቻ ዝንጉነት ታክሎበት መቻል መሪ የሆነበትን ግብ አግኝቷል፡፡ ከአንድ ደቂቃዎች በኋላ መሀል ሜዳ ላይ ድሬዎች ኳስን ባስጀመሩበት ቅፅበት በፈጣን መልሶ ማጥቃት የተነጠቁትን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ደርሷት ኳሷ ዓየር ላይ እያለች በግሩ የግራ እግር ቮሊ ከመረብ አሳርፋው የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች፡፡
ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ሲቀጥል ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሜዳ ላይ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴን አሁንም መመልከት የቻልን ሲሆን ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ጨዋታ ቅኝት ገብቶ አቻ ለመሆን በተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ ቢችሉም የኋላ መስመራቸውን በመድፈን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲታትሩ የነበሩት መቻሎች ከዕረፍት በፊት ባገኟቸው ሁለት ጎሎች ጨዋታው 2-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ የመቻሏ አጥቂ ሴናፍ ዋቁማ የጨዋታው ምርጥ በመባል ተመርጣለች፡፡
8 ሰዓት ሲል የዕለቱ ሁለተኛ መርሀግብር ይርጋጨፌ ቡናን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቷል፡፡ የይርጋጨፌ ቡና የበላይነት በሙሉ ዘጠና ደቂቃው ጎልቶ መታየት በቻለበት በዚህ ጨዋታ በተደጋጋሚ ከሚሻገሩ ኳሶች ዕድሎችን አግኝቶ ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት ሰምሮ በቀዳሚው የጨዋታ አርባ አምስት 19ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አግኝተዋል፡፡ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ አማካዩዋ ስመኝ ምህረት በግንባር ገጭታ በማስቆጠር የእንዳልካቸው ጫካን ቡድን መሪ አድርጋለች፡፡ ከራሳቸው ሜዳ ኳስን በመጀመር ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ሽግግር ሲያደርጉ ድክመት የሚታይባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ በተወሰደባቸው ብሎጫ 59ኛው ደቂቃ ዳግማዊ ሰለሞን ግሩም ሁለተኛ ግብ አክላ ጨዋታው በይርጋጨፌ ቡና የ2ለ0 ውጤት ተደምድሟል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለይርጋጨፌ ቡና ሁለተኛ ግብ ያስቆጠረችው ዳግማዊ ሰለሞን የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡
የሳምንቱ የመጨረሻ መርሀግብር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ እና አዳማ ከተማ መካከል የተከናወነ ነበር፡፡ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ደካማ አቋምን እያሳየ የነበረው የአሰልጣኝ ዮናስ ወርቁ ንፋስ ስልክ ዛሬም በሜዳ ላይ በነበረው ደካማ አቋም የተነሳ ተሽሎ በቀረበው አዳማ ከተማ ፍፁም ተበልጦ 4ለ0 ተሸንፏል፡፡ ከሁለቱ የመስመር ስፍራዎች በመነሳት በተጋጣሚያቸው ላይ ጥቃት በተደጋጋሚ ሲሰነዝሩ የታዩት አዳማዎች 12ኛው ደቂቃ ላዬ ሔለን መሰለ ከመረብ ባሳረፈችው ግብ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ብልጫ ወስደው ጨዋታውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች 25ኛው ደቂቃ ሳባ ኃይለሚካኤል ከማዕዘን ኳስን ስታሻማ ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ ከመረብ ተገናኝታ የአዳማን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች፡፡ 33ኛው ደቂቃ ላይ ሔለን እሸቱ ከዕረፍት መልስ ትዕግስት ዘውዴ ተጨማሪ ጎሎችን አስቆጥረው ጨዋታው 4ለ0 የአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተገባዷል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የአዳማዋ አጥቂ ሔለን እሸቱ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡