በቴዎድሮስ ታደሰ
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ተሳታፊ የሆነው ጅማ አባ ቡና የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የነባሮችን ውልም አራዝሟል፡፡
በከፍተኛ ሊጉ ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ጂማ አባ ቡና የቀድሞውን የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤልን በዋና አሰልጣኝነት ፣ አሰልጣኝ ጋሻው መኮንን እና ይስሀቅ ረጋሳን በምክትል አሰልጣኝነት መቅጠሩ የሚታወስ ነው። ከአሰልጣኝ ቅጥር ባለፈ ክለቡ ለዘንድሮ ውድድር ዘመንም ሃያ አዳዲስ ተጫዋቾችን በይፋ አስፈርሟል።
በዚህም መሰረት አምና በስልጤ ወራቤ በአማካይ እና በአጥቂ ስፍራ የተጫወቱት ዘላለም አበበ እና ርኾቦት ሰለሎን ፣ የድሬደዋ ፖሊስ አመካይ ተጫዋች የነበሩትን እስጢፋኖስ ብርሃኑ እና ግሩም ኩሩጌታን ፣ ከነቀምት ከተማ ግብ ጠባቂው ሌሊሳ ታዬን እና አጥቂው ምስጋና መኮንን የበደሌ ከተማ አጥቂ የነበሩትን ሙሣ ተካ እና እስጢፋኖስ ተማምን ፣ የሀላባ ከተማ አጥቂ የነበረው ጃፈር ከበደን ፣ የአዳማ ከተማ ተከላካይ አካሉ አበራን ፣ የደቡብ ፖሊሱን አማካይ ብሩክ ዳንኤልን ፣ የጋሞ ጨንቻውን አማካይ በረከት ተሾመን ፣ የአርሲ ነገሌው አጥቂ ሰይፉ ተክሉን ፣ ስንሻው ናስርን ከጎሬ ከነማ ፣ ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሔርን ከገላን ከተማ እና ብሩክ ዮሐንስን ከኦዳ ሁሌሆስፒታል ወደ ስብስቡ ቀላቅቋል።
ከአዲስ ፈራሚዎች በተጨማሪ የሦስት የነባር ተጫዋቾችንም ውል ያደሰው ጅማ አባ ቡና ወድድሩ ወደሚጀምርባት ባህር ዳር ከተማ ሲያመራ አዲሱ አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደተዘጋጁ እና ክለቡን ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ እንደተዘጋጁ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።