ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና እና ለገጣፎ ለገዳዲ ነጥብ ተጋርተዋል

ቡናማዎቹ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር አንድ ነጥብ ተጋርተዋል።

በፋሲል ከነማ ሦስት ለምንም ተረተው ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጁት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ታምራት አየለ እና ኢብሳ በፍቃዱ የበረከት ተሰማን እንዲሁም ካርሎስ ዳምጠውን ቦታ ተረክበዋል። ከአራት ለሁለቱ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎችም በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አከናውነዋል። በግብ ጠባቂው እስቄል ሞራኬ እና ወልደአማኑኤል ጌቱ ምትክ በረከት አማረ እና ኩዋኩ ዱሀ ወደ ቀዳሚው አሰላለፍ ገብተዋል።

እምብዛም ሙከራዎች ባልበረከቱበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ8 እና 9ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሁለት ዕድሎች ተፈጥረውበታል። በቅድሚያ ለገጣፎ ለገዳዲ የቡና ተከላካዮች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅመው በመሐመድ አበራ አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረው የተመለሱ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ቡናዎች ኃይለሚካኤል አደፍርስ ከግራ መስመር ባሻገረው እና ብሩክ በግንባሩ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሚኪያስ ዶጂ በመለሰው አጋጣሚ ተከታታይ ሙከራዎች ተደርገዋል።

ተመልካችን ቁጭ ብድግ ማስባል ሳይችል የቀጠለው ጨዋታው በቀጣዮቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች አንድም የሰላ ጥቃት አልተደረገበትም። ኢትዮጵያ ቡና በሚታወቅበት የኳስ ማንሸራሸር አጨዋወት ሲንቀሳቀስ ለገጣፎ ደግሞ በቁጥር በርከት ብሎ ወረድ በማለት ክፍተቶችን እየዘጋ በሚገኙ አጋጣሚዎች ብቻ በፈጣን ሽግግር ለመሄድ ሲጥር ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደተጀመረ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ሲጫወቱ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት በ50ኛው ደቂቃ መባቻ ላይ አግኝተዋል። መዝገቡ ቶላ በራሱ ሳጥን ጥፋት ሰርቶ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም ሮቤል ተ/ሚካኤል ተጠቅሞት ቡድኑን መሪ አድርጓል። 

የኢትዮጵያ ቡና መሪነት ግን ከሁለት ደቂቃዎች በላይ መቆየት አልቻለም። በዚህም ጥፋት ሰርቶ ቡድኑ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት ያስገኘው መዝገቡ ቶላ ወዲያው ጥፋቱን የሚያርምበት ዕድል አግኝቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካይ በማስገባት የቅርፅ ለውጥ አድርጎ በ4-3-3 አደራደር መጫወት ጀምሯል። ለገጣፎ በበኩሉ የመስመር አጥቂ በማስወጣት የመሐል አጥቂ ጨምሮ የበለጠ ቀጥተኛ አጨዋወትን መተግበር ሲሞክር ተስተውሏል። ጣፎዎች ግቡን ካገኙ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ተፈራ አንለይ ከቀኝ መስመር አሻምቶ ኢብሳ በግንባሩ በሞከረው ኳስ ለሁለተኛ ግብ ቀርበው ነበር። ከኳስ ውጪ በወረደ አደረጃጀት ሲጫወቱ የነበሩት ቡናማዎቹ በ68ኛው ደቂቃ ወደ መመራት ተሸጋግረዋል። በዚህም መሐመድ አበራ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን በማታለል ተቀይሮ ለገባው ካርሎስ ዳምጠው ሲሰጠው ግዙፉ አጥቂ ለኢብሳ በፍቃዱ አመቻችቶለት ጥብቅ ኳስ መረብ ላይ አርፏል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ያላቸውን ኃይል በመጠቀም ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን አብዝተው ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል። በ85ኛው ደቂቃ ብሩክ ከመስመር የተሻማን ኳስ ወደ ግብ የሞከረው እና ከደቂቃ በኋላ ሔኖክ ድልቢ ከቅጣት ምት በቀጥታ በመታው ኳስ ለአቻነት ቢንደረደሩም አልተሳካላቸውም። በቀጣይም ግልፅ የግብ ዕድል አግኝተው በወረደ አጨራረስ አምክነዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ የዕለቱ ዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ቅፅበት ኢትዮጵያ ቡና ቀይሮ ወደ ሜዳ ባስገባው የመስመር አጥቂ አንተነህ ተፈራ ጎል አንድ ነጥብ የሚያገኝበትን ዕድል አግኝቶ ጨዋታው አቻ ተጠናቋል።