የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 2-2 ለገጣፎ ለገዳዲ

👉”ተጫዋቾቼ ጨዋታውን ገድለውት መውጣት ይችሉ ነበር” ጥላሁን ተሾመ

👉”ሊስተካከል የሚችል እና ሊያድግ የሚችል ቡድን እንዳለኝ አምናለሁ” ተመስገን ዳና

አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ – ለገጣፎ ለገዳዲ

ስለ ጨዋታው…

ጥሩ ነው ጎል ጋር ደርሰናል። አሁንም ኳስ መጨረስ አልቻልንም። መሐመድ የሳታት ኳስ በጣም የምታስቆጭ ነች። ምን እንደሆነ አልገባንም ፤ ዕድለኞች አይደለንም።

ስለ አሰላለፉ ለውጥ…

በግል ጉዳይ ችግር ያለባቸው ተጫዋቾች ነበሩ። እነሱን አሳርፌ ሌሎች አዳዲስ ተጫዋቾችን ተጠቅሚያለሁ ፤ እነ ኢብሳን እና አንዋርን ተጠቅሚያለሁ ፤ እንደፈለግኩት ተጫውተውልኛል።

በመጨረሻ ደቂቃ ስለሚያስተናግዱት  ጎል…

አዎ! ከልምድ የሚመጣ ነገር ነው ፤ ተጫዋቾቼ ጨዋታውን ገድለውት መውጣት ይችሉ ነበር። ባለቀ ሰዓት ትኩረታችንን ሁሉ እያጣን ነው። ያው ከልምድ ማነስ ነው። ዋጋ አስከፍሎናል።

በቡድኑ እንቅስቃሴ ደስተኛ ስለመሆናቸው…

አዎ! ግን አሸንፈን ብንወጣ ለደጋፊዎቻችን በጣም ጥሩ ነበር። ብዙ ሰው እያስጨነቅን እንደሆነ አውቃለሁ። አሁንም ከትልቅ ክለብ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነው የተጫወትነው ትልቅ ውጤት ነው ፤ ደስ ብሎኛል።


አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ኢትዮጵያ ቡና

በጨዋታው ስላለው አስተያየት…

ለገጣፎ እየተሸነፈ የመጣ ቡድን ቢሆንም በየጨዋታው የሚያሳየው ጠንካራ አቋም መዘጋጀት እንዳለብን ነግሮናል። እንደዚህ ዓይነት ቡድኖች እጅግ በጣም አስቸጋሪዎች ናቸው። ይሄንንም ነገር ነው ሜዳ ላይ የተመለከትነው። ጨዋታው እጅግ በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነበር።

በጨዋታው ቡድኑ ላይ ስለነበረው ክፍተት…

ተጋጣሚያችን በጨዋታ ፍላጎት እና እያንዳንዱ የሜዳ ክፍል ላይ የእኛ ተጫዋቾች እንዳይንቀሳቀሱ በማድረጉ ረገድ በመጀመሪያ አጋማሽ የተሻለ ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ ላይም ነገሮችን ለመቀየር ሞክረናል ፤ የተወሰኑ ለውጦችም ተመልክተናል። ቀድመን ግብ ብናስቆጥርም ያንን ግብ ማቆየት አልቻልንም። በአጠቃላይ ዛሬ ከነበረው እንቅስቃሴ መነሻነት ጨዋታው አቻ መጠናቀቁ መጥፎ አይደለም። ምክንያቱም ለገጣፎዎች ዛሬ ጥሩ ነበሩ። ስለዚህ ጣፎ በመጀመሪያው አጋማሽ በነበረው እንቅስቃሴ እና እኛ በሁለተኛው አጋማሽ ካደረግነው ነገር አንፃር አቻ ፍትሀዊ ነው።

ስለጫና…

እንደሚታወቀው በርካታ ተጫዋቾች ወጣቶች ናቸው። በአቅም ረገድ ጥሩ ይሁኑ እንጂ ገና በትልቅ ደረጃ መጫወት የሚችሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ አይደሉም። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በጣም ትልቅ ቡድን ነው። የዚህን ቡድን ኃላፊነት ተሸክሞ መጫወት በጣም ከባድ ነው። ምናልባት ተጫዋቾቼ እዛ ጫና ውስጥ ይገኛሉ ብዬ ነው የማምነው ፤ በግሌ ግን ምንም ጫና የለብኝም። ሊስተካከል የሚችል እና ሊያድግ የሚችል ቡድን እንዳለኝ አምናለው።