ሪፖርት | አዞዎቹ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ በሆነው ፍልሚያ አርባምንጭ ከተማ አዳማ ከተማን ረቷል።

በ9ኛ ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር ያለ ግብ የተለያዩት አርባምንጭ ከተማዎች አቡበከር ሸሚል እና መላኩ ኤልያስን በቡጣቃ ሸመና እና ሱራፌል ዳንኤል ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በባህር ዳር ከተማ ከተሸነፉበት ቀዳሚ ስብስብ ደስታ ዮሐንስ ፣ ዳንኤል ደምሴ ፣ ዊሊያም ሰለሞን እና አቡበከር ወንድሙን አሳርፈው ጀሚል ያዕቆብ ፣ ፍሬድሪክ አንሳ፣ ቢኒያም አይተን እና ቦና ዓሊን በቀዳሚ አሰላለፋቸው አካተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራስ ለማድረግ ሁለቱ ቡድኖች ጠንከር ያለ ትግል ማሳየት የጀመሩ ሲሆን በአንፃራዊነት አዳማ ከተማ የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሱ አድርጎ ሲጫወት ነበር ፤ አርባምንጭ ደግሞ ፈጣን ሽግግርን እና ተሻጋሪ ኳሶችን ለመጠቀም ሲጥር ተስተውሏል። ሩብ ሰዓት እንደሞላም አዞዎቹ የመጀመሪያ ሙከራ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ሙና በቀለ ሰንዝሮላቸዋል በ18ኛው ደቂቃ ደግሞ መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። በዚህም አህመድ ሁሴን ሱራፌል ዳንኤል ከመዓዘን ምት ያሻማው ኳስ በተከላካዮች ተገጭቶ ሲመለስ ሳጥኑ መግቢያ ላይ አግኝቶት በድንቅ አጨራረስ መዳረሺያውን መረብ ላይ አድርጎታል።

ጨዋታው በሚፈልጉት መልኩ የቀጠለላቸው አርባምንጮች አሁንም በቀጥተኛ ኳስ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም 30ኛው ደቂቃ ላይ አዩብ በቀታ ከራሱ ክልል በረጅሙ የመታውን ኳስ አሸናፊ ኤልያስ ደርሶበት በቀጥታ መጥቶት ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ አውጥቶታል። ሰዒድ ያወጣውን ኳስ ከመዓዘን ሲሻማ ደግሞ ራሱ አዩብ በግንባሩ የግብ ምንጭ ሊያደርገው ጥሮ ዒላማውን ስቶበታል። አዳማዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር አጋማሹን ቢከውኑም የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ተስኗቸው እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ አዳማዎች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስገባት ተቀዛቅዞ የነበረውን የፊት መስመር ለማነቃቃት ጥረዋል። 50ኛው ደቂቃ መግቢያ ላይም በአጋማሹ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አሜ መሐመድ ጥሩ ዕድል ፈጥሮ በተከላካዮች ተመልሶበታል። 55ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ይበልጥ ጨዋታውን የሚዘውሩበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። በዚህም በ34ኛው ደቂቃ ጥፋት ሰርቶ የቢጫ ካርድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት የነበረው ቡጣቃ ሸመና ከ20 ደቂቃዎች በኋላ ሌላ ጥፋት ሰርቶ በሁለት ቢጫ ከጨዋታው በቀይ ካርድ ወጥቷል።

የቁጥር ብልጫውን ለመጠቀም መጣር የጀመሩት አዳማዎች በ59ኛው ደቂቃ ቢኒያም አይተን የግል ጥረቱን ተጠቅሞ በመታው ኳስ አቻ ሊሆኑ ነበር። አርባምንጮች በበኩላቸው በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት ከቀይ ካርዱ በኋላ ወዲያው የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስወጣት ጨዋታውን የሚቆጣጠሩ እና ክፍተቶችም የሚዘጉ ተጫዋቾች አስገብተው ጨዋታውን ለመቀጠል ወጥነዋል።

70ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማ ከጨዋታው አቻ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ፍሬ ሊያፈራ ተቃርቦ ነበር። በዚህም ዳዋ ሆቴሳ ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ መትቶት ለጥቂት ወጥቶበታል። በቀሪ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ የጠራ የግብ ዕድል ሳይፈጠር ፍልሚያው በአርባምንጭ ከተማ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ያጋሩ