የአሠልጣኞች አስተያየት | አርባምንጭ ከተማ 1-0 አዳማ ከተማ

👉”ጥሩ ቀን ነው ያሳለፍነው” መሳይ ተፈሪ

👉”በእርግጠኝነት ይሄ ቡድን አሁን ካለበት ወጥቶ የተሻለ ነገር ይዞ ይጨርሳል ብዬ በሙሉነት መናገር እችላለሁ” ይታገሱ እንዳለ

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

እግዚአብሔር ረድቶናል። የተወሰኑ ጨዋታዎችን ውጤት ሳንይዝ ነበር የመጣነው። መጀመሪያው አጋማሽ ላይ ለማጥቃት ጥረት አድርገን ጎል አስቆጥረን ከዛ በኋላ ውጤቱን በጥንቃቄ ይዘን ወጥተናል። ውጤቱ በጣም ያስፈልገን ነበር ብዙ ደረጃ ነው የምናሻሽለው። ቀሪ ጨዋታ አለ ፤ ያሉ ነገሮች መልካም ነው የሚሆኑት። በአጠቃላይ ዛሬ ያገኘነው ሦስት ነጥብ ከተወሰኑ ጨዋታዎች በኋላ የተገኘ ነው። በተለይ ድሬዳዋ ከመጣን በኋላ ሜዳ ላይም ግብ እንዳይቆጠረብን እያደረግን የነበረን አቅም ጠንካራ ነው። ዛሬም ተጫዋቾች ያሳዩት ጥሩ ነገር ነው።

ውጤት ለማስጠበቅ ስለተከተሉት መንገድ…

ቴክኒካሊ የሄድንባቸው ነገሮች ጥሩ ነበሩ። 5-3-1 ነው ያደረግነው ጥሩ ቡድን ነው።

ስለነበረው የውጤት ረሃብ…

በጣም በጣም ተርበን ነበር ፤  እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሆነ ነው ይሄንንም ያየነው። እኛ ባለፍንበት መንገድ የሌሉ የተለያዩ ነገሮች አሉ። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለነበር እውነት ለመናገር በጣም ደስ ብሎናል ፤ ጥሩ ቀን ነው ያሳለፍነው። ብዙ የሚከፈቱ ነገሮች ይኖራሉ በራስ መተማመን ስለሚጨምርልን።

ባለፉት ጨዋታዎች ውጤት ማጣት ስለፈጠረባቸው ጫና…

ብዙም የተለየ ጫና ውስጥ አልገባም። ግን ባቀድነው ልክ ሄደናል። ከቡና ጋር ተጫውተን ቀጥሎ ከጊዮርጊስ ቀጥሎ ከፋሲል እነዚህ እነዚህ ጠንካራ ጨዋታዎች ነበሩ። ውጤት ይዘን ነው የወጣነው አንድ አንድ ነጥቡ ቀላል አልነበረም። ከዚህ ላይ ቀጣይ ስንጨምር በደንብ ወደፈለግንበት መሄድ እንችላለን። ውጤት ሲጠፋ ሀሳቦች ይኖራሉ ግን ብዙም የወጣ ጭንቀት የለም።

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው እንደተለመደው ነው ፤ ዛሬም ማሸነፍ አልቻልንም። ከመሸነፍ ለመውጣት ተጫዋቾችም ላይ ጫና አለ ፤ ጭንቀት አለ። ያንን ነገር በሚቀጥለው አሻሽሎ መጥቶ ወደ ማሸነፍ መንገድ መግባት ነው፡፡

በተደጋጋሚ ቀድሞ ግብ ስለ ማስተናገድ…

የትኩረት ማነስ ነው፡፡ የተመለሰ ኳስ ነው አሁንም የገባብን የትኩረት ማነስ ነው። በተደጋጋሚ ጎሎች እንደዚህ ነው እየገቡብን ያለው ፤ ከገቡብን በኋላ የምንከፍለው መስዋዕትነት ሳይገባብን ብንከፍላቸው ጥሩ ነበር፡፡ ከገባብን በኋላ ግን የምናባክነው ጉልበት የምንከፍለው መስዋዕትነት ከመግባቱ በፊት ቢሆን የበለጠ አዋጭ ይሆን ነበርና በመሸነፍ ውስጥ መጠንከር አለ ፤ አሁንም ተጫዋቾች የሚችሉትን ነገር ነው ያደረጉት ጨዋታም ገና ስለሆነ በእርግጠኝነት ይሔ ቡድን አሁን ካለበት ወጥቶ የተሻለ ነገር ይዞ ይጨርሳል ብዬ በሙሉነት መናገር እችላለሁ፡፡ አንዳንዴ የጨዋታው ሁነት እስከ ሚቀየር ድረስ ስትሸነፍ ስትሸነፍ የሚይዝህ ነገር አለና ተጫዋቾቹም ላይ ጫና ኖሮባቸው ነው የሚገቡት። አቻ ወጥተክ ካልቀየርክ በስተቀር ለማሸነፍ ብለህ እየገባህ እንደዚህ አይነት መስዋዕትነት ይከፈላል። ተጫዋቾቹም ለማሸነፍ ነው የሚገቡትና አንዳንዴ አቻም ወጥተህ ሪትምህን ማስተካከል አንድ ነገር ነው ፤ ያንን ደግሞ እናስተካክላለን ብዬ አስባለሁ፡፡

የሰው ቁጥር ብልጫን ስላለመጠቀማቸው…

አሉን የምንላቸውን አጥቂዎች ነው ያስገባነው። እንደምታየው አርባምንጭ በመከላከል ይታወቃል ፤ ጥቅጥቅ ብለው ነው የሚከላከሉት። ያንን ሰብሮ ለመግባት ከብዶናል። ይሄ ደግሞ ቅድም እንዳልኩት ከጉጉት የመጣ ነውና አሁንም ተረጋግተን ወደ ሚፈለገው ሪትም እስክንመጣ ድረስ ጠንክረን መስራት ነው የሚጠበቅብን፡፡

ያጋሩ