ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ወሳኝ ድል በመቀዳጀት ነጥባቸውን ሁለት አሀዝ አስገብተዋል

ወላይታ ድቻ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ዘላለም አባተ ብቸኛ ግብ ፋሲል ከነማን አሸንፏል።

ወላይታ ድቻ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈበት ጨዋታ አንፃር በግብ ጠባቂነት ቢኒያም ገነቱን በወንድወሰን አሸናፊ ምትክ ሲጠቀም ያሬድ ዳዊት እና ዘላለም አባተም በደጉ ደበበ እና ንጋቱ ገብረስላሴ ተተክተዋል። ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ለጨዋታው የቀረቡት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ በአስቻለው ታመነ ፣ አምሳሉ ጥላሁን እና ታፈሰ ሰለሞን ቦታ መናፍ ዐወል ፣ ወንድምአገኝ ማርቆስ እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን ወደ ቀዳሚው አሰላለፍ አስገብተዋል።

በኳስ ቁጥጥር ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያሰቡት ፋሲል ከነማዎች ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በፈጣን ቅብብል የወላይታ ድቻ ግብ ክልል ደርሰው ነበር። በዚህም ፍቃዱ ዓለሙ በተከላካዮች መካከል በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም ሲጥር መልካሙ ቦጋለ ከደጉ ደበበ ጋር ታግሎ አምክኖበታል። በተቃራኒው ወደ ራሳቸው ግብ ወረድ ብለው መንቀሳቀስን የመረጡት ወላይታ ድቻዎች ዘለግ ያለውን ደቂቃ በራሳቸው ሜዳ ቢያሳልፉም በቀጥተኛ አጨዋወት እና ፈጣን ሽግግር ፋሲልን ለመፈተን ጥረዋል። በ17ኛው ደቂቃም ሳሙኤል ተስፋዬ በሞከረው የቅጣት ምት ለመጀመሪያ ጊዜ ጠንከር ያለ ሙከራ ያስመዘገቡበትን ሁነት አስመልክተዋል።

በዚህኛው የጨዋታ አጋማሽ እምብዛም የጠሩ የግብ ሙከራዎች ባይስተናገዱም በቀጣዩ ደቂቃ ግብ አስቆጣሪ የሚመስለው ቡድን ፋሲል ከነማ ነበር። ምንም እንኳን ቡድኑ የፈጠራ አቅማቸው የተሻሉ ተጫዋቾችን አብዝቶ ወደ ሜዳ ቢገባም ጠጣሩን የድቻ የኋላ መስመር መስበር አልቻለም። ይህንን ተከትሎም ከሳጥን ውጪ በርካታ ጥቃቶችን ሲሰነዝር ታይቷል። በተለይ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የነበረው ሱራፌል ሁለት ጥሩ ዒላማቸውን የጠበቁ ጥቃቶችን ቢሰነዝርም ግብ ጠባቂው ቢኒያም አድኖበታል። እንደተገለፀው ቀጥተኛ አጨዋወትን ሲተገብሩ የታዩት ድቻዎች ከግማሽ ሰዓት በኋላ የተሻለ ለግብ የቀረቡበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። በቅድሚያ በ31ኛው ደቂቃ ሀብታሙን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ቃልኪዳን ሲሞክር በ44ኛው ደቂቃ ደግሞ ስንታየሁ ከሳጥን ውጪ ጥቃት ሰንዝሮ መክኖበታል።

ፋሲሎች ሁለተኛውን አጋማሽም በፈጣን ጥቃት ነበር የጀመሩት። በ48ኛው ደቂቃም ሽመክት ረጅም ርቀት ኳስ እየገፋ ተጫዋች በመቀነስ ሳጥን ውስጥ በመግባት የሞከረው የጨዋታው ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ መጨረሻው መረብ ሳይሆን ቀርቷል። ድቻዎች በአንፃሩ የአጨዋወት ለውጥ ሳያደርጉ በሚደነቅ የመከላከል ዲሲፕሊን መንቀሳቀሳቸውን ቀጥለዋል።

ከመጀመሪያው የሽመክት ሙከራ በኋላ ጨዋታው ቀጣዩን ሙከራ ለማስተናገድ በርከት ያሉ ደቂቃዎች ወስደውበታል። ነገር ግን ቀጣዩ ሙከራ ግብ ሆኖ መሪ ተገኝቷል። በዚህም በ67ኛው ደቂቃ በኃይሉ ተሻገርን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዘላለም አባቴ የሜዳውን ሳር ከረገጠ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ከግራ መስመር የተሻማን ኳስ በአንድ ንክኪ ከመረብ ጋር አዋህዶት ድቻ ቀዳሚ ሆኗል። ድቻ ይህቺን ግብ ካስቆጠረ በኋላም በሚገርም ተነሳሽነት በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት ሲጣጣር ተስተውሏል።

ፋሲል ከነማዎች ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ወዲያው የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች በማስገባት በተሻለ ወደፊት ለማምራት ቢጥሩም ውጤታማ መሆን አልቻሉም። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ግን ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ወደ ግብነት ሊቀይሩ ተቃርበው አናጋው ባደግ ውጥናቸውን አምክኗል። ፍልሚያው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አካላዊ ጉሽሚያዎች በዝተውበት የነበረ ሲሆን ቃልኪዳን እና ኪሩቤልም በሁለቱም ቡድኖች በኩል በጭማሪው ደቂቃ መባቻ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጡ ሆኗል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።