የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ ፣ ልደታ እና አዲስ አበባ ወሳኝ ድል አሳክተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲጀመር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ልደታ ክፍለከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ሙሉ ነጥብ ሸምተዋል፡፡

የዕለቱ ቀዳሚ የነበረው ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል የተደረገ ነበር፡፡ ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን ባስተዋልንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመሀል ሜዳ ከሰናይት እና ብርቱካን ጥምረት በሚነሱ ኳሶች ንግድ ባንኮች ብልጫን በመውሰድ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው ጫና ፈጥረዋል፡፡

የንግድ ባንክ ስህተት በመጠበቅ በረጃጅም ኳሶች በተለይ አጥቂዋ ቤተልሄም ታምሩን ማዕከል አድርገው ለመጫወት ቢሞክሩም ተከላካዮችን አልፈው ለማስቆጠር ይሳናቸው የነበሩት እንስት አዞዎቹ በተቃራኒው 18ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዮች በሰሩት የአቋቋም ስህተት የተነሳ በአረጋሽ ካልሳ ጎል ተቆጥሮባቸዋል፡፡ የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው በማድረግ ጫናዎችን ማሳደራቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች በድጋሚ አረጋሽ ካልሳ የጎል አስቆጣሪነት ደረጃውን በሰባት እንድትመራ ያስቻላትን ግብ አስቆጥራለች።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ ተቃራኒ መልክን የተላበሰ ነበር፡፡ አርባምንጭ ከተማዎች በቀዳሚው አርባ አምስት የተወሰደባቸውን ብልጫ ወደ ራሳቸው መልሰው በተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዘሩ ተስተውሏል፡፡ በተለይ በፈጠሩት ጫና 69ኛው ደቂቃ ላይ የባንኳ የመስመር ተከላካይ ብዙአየው ታደሰ አጥቂዋ ቤተልሄም ታምሩ ላይ በሰራችባት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሷ ቤተልሄም አርባምንጭን ወደ ጨዋታ የምትመልስ አጋጣሚን ብታገኝም ግብ ጠባቂዋ ንግስቲ መዓዛ መልሳባታለች፡፡ ጨዋታውም ከዕረፍት በፊት በተቆጠሩ ጎሎች በንግድ ባንክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

8 ሰዓት ሲል የአዳማ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተማ ሁለተኛ መርሃግብር ጅምሩን አድርጓል፡፡ ፈጠን ባለ አጀማመር ቢጀምርም በሒደት አሰልቺ የነበረ ፍሰትን የተመለከትንበት የቡድኖቹ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ የነበራቸው ልደታዎች አሰገደች ሸጎ በተቃራኒው ለአዳማ ተሰልፋ የምትጫወተው እህቷን ሰናየት ሸጎን በድንቅ ብቃት በማለፍ 33ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ አስገራሚ ጎልን ከመረብ አሳርፋ ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የቡድኖቹ ጨዋታ ቀጥሎ ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክርን ሜዳ ላይ አስመልክቶናል፡፡ በዚህም 64ኛው ደቂቃ ሳባ ኃይለሚካኤል ባስቆጠረችው ጎል አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታ ቢመለሱም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ያህል መደበኛ ደቂቃዎች ሲቀሩ ህዳት ካሱ የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ ፎዚያ ዝናቡ የግብ ክልሏን ለቃ በወጣችበት ቅፅበት ሁለተኛ ጎል ከመረብ አዋህዳ ጨዋታው በመጨረሻም በልደታ ክፍለ ከተማ 2-1 ድል አድራጊነት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዲስ አበባ ከተማን ያገናኘው የ10 ሰዓት ጨዋታ ብርቱ የሜዳ ላይ የመሸናነፍ ትግልን ያሳየን ነበር፡፡ ከወትሮው እንቅስቃሴያቸው በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዘው የታዩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በጨዋታው በተጋጣሚያቸው እጅጉን ተፈትነው ተስተውሏል፡፡ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔው ቡድን በተደጋጋሚ ኳስ እና መረብን የሚያገናኙበትን በርከት ያሉ ዕድሎችን ፈጥረው ቢታዩም የአዲስ አበባዋ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ የምትቀመስ አልነበረችም፡፡ በአንፃሩ በተለይም ከዕረፍት መልስ የኤሌክትሪክን ስህተት ለመጠቀም ሲታትሩ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች መዲና ጀማል 68ኛው ደቂቃ ከመረብ ያሳረፈቻትን ግብ አስጠብቀው 1-0 ማሸነፍ ችለዋል።

ያጋሩ