በቶማስ ቦጋለ እና በጫላ አቤ
ትናንት የጀመረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬም በ11 ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል ስድስቱ ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል።
የ03:00 ጨዋታዎች
ባህር ዳር ላይ በምድብ ‘ሀ’ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የባቱ እና ጅማ አባ ቡና ጨዋታ ያለግብ የተቋጨ ነበር። ጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩ ብርቱ ፉክክር ቢስተዋልበትም አልፎ አልፎ ባቱዎች ወደፊት እየተጠጉ ከሚያደርጉት ሙከራ ውጪ በግብ ሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። በተለይም 62ኛው ደቂቃ ላይ የባቱ ከተማው አምበል ክንዳለም ፍቃዱ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ሞክሮት የግራውን ቋሚ ታክኮ ለጥቂት የወጣው ኳስ በጨዋታው የተሻለ ሙከራ ነበር።
ጅማ ላይ በምድብ ‘ለ’ ቦዲቲ ከተማ አቦነህ ገነቱ በ33ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ጎል ሲመራ ቢቆይም ብሩክ ቸርነት አምቦን 73ኛው ደቂቃ ላይ አቻ አድርጎ ጨዋታው 1-1 ተፈፅሟል። ያለፈው ዓመት ከቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ በተሰናበተው ጅማ አባ ጅፋር እና በሶዶ ከተማ መካከል በሆሳዕና የተካሄደው የምድብ ‘ሐ’ ጨዋታም ተመጣጣኝ ፉክክር እና አልሸነፍ ባይነት ተስተውሎበት ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የ05:00 ጨዋታዎች
በበርካታ ደጋፊዎች እና በብርቱ ፉክክር በታጀበው የምድብ ‘ሀ’ የወልዲያ እና ሰበታ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ዓይነት መልኮች የነበሩት ሲሆን የመጀመሪያዎቹን 20 ደቂቃዎች ሰበታዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል። በተለይም 16ኛው ደቂቃ ላይ ኪዳኔ አሰፋ ወደግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነት የመለሰው ኳስ በሰበታዎች በኩል ውጤቱን ሊቀይር የሚችል ትልቁ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። በግብ ጠባቂው የተመለሰውን ኳስ መነሻ ያደረጉት ወልዲያዎች በሴኮንዶች ልዩነት በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ቀሪዎቹን 25 ደቂቃዎች ወደ ጨዋታው የተመለሱት ወልድያዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢኖራቸውም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው አጋማሹ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ግለት እየጨመረ ሲሄድ ወልዲያዎች እጅግ ተሻሽለው ቀርበዋል። የመጀመሪያውን የተሻለ ዕድል 53ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጀርባ ሆኖ ያገኘው ቢንያም ላንቃሞ በደካማ አጨራረስ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። ባባከነው ዕድል ሳይደናገጥ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረገው ቢያንም 73ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት የሰበታው ዮሐንስ አድማሱ ራሱ ላይ አስቆጥሮ ወልዲያ መሪነቱን ማሳደግ ችሏል። ሰበታ ከተማን ለባዶ ከማሸነፍ የታደገችውን ግብ ተመስገን ገብረኪዳን የግብጠባቂውን ስህተት ተጠቅሞ ማስቆጠር ችሏል።
ጅማ ላይ በምድብ ‘ለ’ በተደረገ ጨዋታ ነቀምት ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመስገን ዱባለ እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ ዳንኤል ዳዊት እና ዘርይሁን ይልማ ባስቆጠሯቸው ግቦች ይርጋጨፌ ቡናን 3-1 ረሯል። ለይርጋጨፌዎች ጨዋታው ሊፈፀም አንድ ደቂቃ ሲቀረው ኢሳያስ ታደሰ ብቸኛውን ጎል ከመረብ አገናኝቷል።
ሆሳዕና ላይ ቡራዩ ከተማ እና ኮልፌ ክፍለከተማ መካከል በተደረገው ጨዋታውም ኮልፌ ትንቅንቅ በተሞላበት መልኩ ማሸነፍ ችሏል። በርከት ያሉ ታዳጊዎችን ይዞ የገባው ኮልፌ በ25ኛው ደቂቃ ላይ በቢኒያም ተስፋዬ ቀዳሚ የሆነ ቢሆንም በሁለት ደቂቃ ልዩነት ፍቃዱ አሰፋ ቡራዩ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል። ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ኮልፌዎች በ36ኛው ደቂቃ ድጋሚ መሪ ያደረጋቸውን ግብ በብሩክ ሰሙ አማካኝነት አግኝተዋል።
እንደመጀመሪያው አጋማሽ ፈጣን አጨዋወት እና ቶሎ ቶሎ ግብ ላይ መድረስ በታየበት የሁለተኛው አጋማሽ በ59ኛው ደቂቃ ስንታየው ሰለሞን ግብ በማስቆጠር የኮልፌን መሪነት ማጠናከር ችሏል። ጨዋታው በዚህ መልኩ በመደበኛ ደቂቃ የቀጠለ ቢሆንም በተጨመረው 3 ደቂቃ በተገኝው የፍፁም ቅጣት ምት ሲሳይ ዋጁ ቡራዩ ከተማን ከሽንፈት ያላዳነችውን ግብ በማስቆጠር ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል።
በጨዋታው ቀልብ ስበው የነበሩት የኮልፌ ወጣቶች ብሩክ ሰሙ እና ስንታየው ሰለሞን ለቡድናቸው አመርቂ እንቅስቃሴ ያረጉ ሲሆን በሦስቱ ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራቸው።
የ08:00 ጨዋታዎች
መጠነኛ ፉክክር በታየበት የቡታጅራ እና ሀላባ የመጀመሪያ አጋማሽ ቡታጅራዎች ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ ቢቸገሩም በተደጋጋሚ የተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ግን መድረስ ችለዋል። የቡታጅራው መሐመድ ሁሴን በጨዋታው መሀል እግሩ ላይ ወደ ሆስፒታል እንዲያመራ ያደረገ ከባድ ጉዳት አስተናግዷል። ከዕረፍት መልስ 68ኛው ደቂቃ ላይ ክንዴ አብቹ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ በድኑን መሪ ማድረግ ቢችልም በ5 ደቂቃዎች ልዩነት ተቀይሮ የገባው የሀላባው ተጫዋች ሐብታሙ በየነ ባስቆጠረው ግብ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።
በምድብ ‘ለ’ ከፕሪምየር ሊጉ የአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የተመለሰው አዲስ አበባ ከተማ ዓመቱን በድል የጀመረበትን ውጤት አስመዝግቧል። ተጋጣሚው ካፋ ቡና 39ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ቢሆንም ከዕረፍት መልስ ሮቤል ግርማ እና ሙሉቀን ታሩኩ የመዲናዋን ክለብ አሸናፊ ያደረጉ ግቦችን አስቆጥረዋል።
10:00 ጨዋታዎች
ባህር ዳር ላይ በምድብ ‘ሀ’ የመጨረሻ ጨዋታ ዱራሜ እና ወሎ ኮምቦልቻ ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል ወሎ ኮምቦልቻዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ከዕረፍት መልስ ግን ተመጣጣኝ ፉክክር ተስተውሎበታል። ጨዋታው ለዐይን ማራኪ በሆኑ ቅብብሎች ቢታጀብም ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል።
ጅማ ላይ የሚከናወነው የምድብ ለ ጨዋታ በመጨረሻ ባስተናገደው የዛሬ ጨዋታ ከንባታ ሹንሺቾ 9ኛው ደቂቃ ላይ ውበት አብተው ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ እንደአዲስ የተመሰረተው ንብን ማሸነፍ ችሏል።
ሆሳዕና ላይ በዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ ኦሜድላን ከደሴ ከተማ አገናኝቶ 1-1 ተጠናቋል። በሁለቱ አጋማሾች ሁለት ዓይነት መልክ ባሳየን ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኦሜድላ የበላይነቱን የወሰደ ሲሆን ጨዋታው በጀመረ በ6ኛው ደቂቃ በተመስገን መንገሻ አማካኝነት መሪ ሆኗል።
በሁለተኛው አጋማሽ ደሴ ከተማ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለ ሲሆን በ61ኛው ደቂቃ የኦሜድላ ግብ ጠባቂ በራሱ ግብ ክልል ውስጥ በሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ማናዬ ፋንቱ በማስቆጠር ደሴ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል።