ደቡብ ፖሊስ የመፍረስ ስጋት ተደቅኖበታል ?

“በበጀት እጥረት የተነሳ ይሄ መሆኑ ያሳዝናል” ኮማንደር ግርማ ዳባ የስፖርት ክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት

“ግራ ገብቶን በካምፕ ውስጥ እንገኛለን” የክለቡ ተጫዋቾች

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በርካታ ተጫዋቾችን ካፈሩ ክለቦች መካከል ይጠቀሳል ፤ በአትሌቲክስ እና በእግርኳሱ ዘርፍ በ1989 ምስረታውን ያደረገው የደቡብ ፖሊስ ስፖርት ክለብ፡፡ ከፖሊስ ሰራዊት በየወሩ ከደመወዝ በሚቆጠረጥ እና አልፎ አልፎ ደግሞ በደቡብ ክልል መንግሥት በጀት እየተመደበለት የዘለቀው ክለቡ በ1990 መባቻ ከፈረሰ በኋላ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በድጋሚ ተመስርቶ ያለፉትን ዘለግ ያሉ ዓመታቶችን በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ እየዘለቀ ቀጥሏል፡፡ ከሚሊኒየሙ መግቢያ ጀምሮ በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን በመያዝ በቀደም የብሔራዊ ሊግ አጠራር በአሁኑ አንደኛ ሊግ በሚባለው ውድድር ላይ ተሳትፎን ካደረገ በኋላ በ1999 ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጎ የሦስት ዓመት የውድድር ታሪክ ኖሮት በ2001 ዳግም ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን በመውረድ ዘጠኝ ዓመታትን በአንደኛ ሊጉ ላይ እና በከፍተኛ ሊግ ሲሳተፍ ቆይቶ በ2010 በድጋሚ ወደ ላይኛው የሀገሪቱ ትልቁ ሊግ በመመለስ የአንድ ዓመት ቆይታ ብቻ ኖሮት በዓመቱ በድጋሚ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ለመውረድ በመገደዱ የተነሳ ሶስት ተከታታይ የውድድር ዘመንን በከፍተኛ ሊጉ እየተወዳደረ ቆይቷል፡፡

ባለፈው የ2014 የውድድር ዘመንን በምድብ ሐ ተደልድሎ በአሰልጣኝ አላዛር መለሰ መሪነት የሦስተኛ ደረጃን በምድቡ በመያዝ የፈፀመው ይህ አንጋፋ ክለብ ዘንድሮም በከፍተኛ ሊጉ ላይ ለተከታታይ አራተኛ ዓመት ለመወዳደር አቅዶ በመስከረም ወር አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የነባር ተጫዋቾችን ውል በማራዘም ያለፉትን ሦስት ወራት ዝግጅት ላይ ቆይቷል። ሆኖም አሁን ላይ ወደ ውድድር ለመግባት አቅቶት እየተንገዳገደ ይገኛል ከዚህም አልፎ ለመፍረስ ስለ መቃረቡ ሰምተናል፡፡ የዘንድሮውን የከፍተኛ ሊግ ውድድር ለመሳተፍ ክለቦች ለዳኞች እና ታዛቢዎች መክፈል ያለባቸውን ክፍያ ከፍለው ለውድድር የቀረቡ ሲሆን በምድብ ሐ በትናንትናው ዕለት ከነገሌ አርሲ ጋር ጨዋታ የነበረው ደቡብ ፖሊስ ግን እስከ አሁን ይሄን ክፍያ ባለመፈፀሙ ጨዋታውን አላደረገም። የክለቡ የመቀጠል ህልውናም አደጋ ላይ ስለመሆኑ ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት አረጋግጣለች፡፡

የክለቡ ተጫዋቾች ለድረ ገፃችን እንዳሉት ከሆነ “ልምምድ እየሰራን ነው አሁንም ግራ ገብቶን በክለቡ ካምፕ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ለውድድር መቅረብ ሲገባን እስከ አሁን ክለቡ ክፍያ ባለመፈጸሙ ወደ ሆሳዕና አልሄድንም። ደመወዛችንን ከ15 ሺህ ወደ 5 ሺህ ተቀንሶ ነበር። እኛ ግን ለክለቡ ብለን ከዚህም ላይ ተቀንሶ እንወዳደር ብንልም መልስ ማግኘት አልቻልንም፡፡ አሁን ዝውውር እንኳን አልቋል ካልተወዳደርን የእኛ ዕጣ ፈንታ አስግቶናል አሁንም ድረስ ግን በክለቡ ካምፕ ውስጥ እንገኛለን”፡፡ በማለት አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡

እስከ አሁን ለውድድር አለመቅረባቸውን የታዘበችው እና የተጫዋቾቹን ጥያቄ መሠረት ያደረገችው ሶከር ኢትዮጵያ ክለቡ የበጀት ዕጥረት ስለገጠመው እስከ አሁን መመዝገብ አለመቻሉ እና እንዳይፈርስ ብሎም ወደ ውድድር እንዲገባ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት ግርማ ዳባን ጠይቀን ተከታዩን ሀሳብ በዝርዝር ነግረውናል፡፡ “የበጀት ችግር አጋጥሞናል ይሔንንም ለመፍታት እየታገልን ነው ፤ በጀት የለንም። የክልሉ መንግሥትም ከዚህ በፊት ይደጉመን ነበር አሁን ላይ በተለያዩ ችግሮች የተነሳ ድጋፍ አላደረገልንም፡፡ እንደ ፖሊስ ኮሚሽን የተወሰነ ብር በጅቷል ውድድር የሚያስጨርስን ግን አይደለም በዚህም የተነሳ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርበናል ምላሽ ግን አላገኘንም፡፡ የበጀት ችግራችን እስኪ ቀረፍ ድረስ ፌዴሬሽኑ ይሄንን እንዲረዳን ነግረናል ፤ ፎርፌ እንዳይሰጥብን። ይሄንን ክፍያ ለመፈፀም እስከ አሁን እየታገለን ነው፡፡ ሰኞ አልያም ማክሰኞ ገብተን መጫወት እንድንችል አግዙን ብለናል ነገር ግን መልስ አላገኘንም።”

“የክልሉ መንግሥት አመራሮች ለስብሰባ አዲስ አበባ ናቸው፡፡ በአካል ማግኘት አልቻልንም ስለዚህ ይሔ ደግሞ ችግር ፈጥሮብናል፡፡ አሁንም ተጫዋቾች ልምምድ እየሰሩ ነው። እንዳይሄዱ ወደ ሌላ ቦታ አድርገናቸዋል ፤ ሂዱ ቢባሉ ራሱ ለመሄድ አስቸጋሪ ነው። በተቻለ መጠን በጀት እየጠበቅን ነው። ዝግጅት ከተጀመረ ሦስት ወር ሆኗል። መስከረም ወር ላይ ጀምረናል ፤ የወዳጅነት ጨዋታም ተደርጓል ለውድድር እንዳንገባ ግን በጀት እንቅፋት ሆኖብናል፡፡ በበጀት እጥረት የተነሳ ይሄ በመፈጠሩ ያሳዝናል፡፡ የክለቡ የገቢ ምንጩ ሰራዊቱ ከራሱ በጀት እየቀነሰ አልፎ አልፎ በክልሉ መንግሥት እየተደጎመ እዚህ ደርሷል ዘንድሮ በጀት የለንም። ማፈረሱ ደግሞ አስቸጋሪ ነው ፤ ከሚመለከተው አካል ውሳኔ ለማግኘት በመጠበቅ ላይ ነን” ሲሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አብራርተውልናል፡፡

እንደ ጌታነህ ጌታነህ ከበደ ፣ ግሩም ባሻዬ ፣ ለዓለም ብርሀኑ ፣ ሔኖክ አየለ እና ሌሎች በርካታ ስመጥር ተጫዋቾችን ያፈራው ክለቡ እስከ አሁን ለውድድር ባለመቅረቡ ቀጣይ ዕጣ ፈንታው ምን እንደሚሆን ይጠበቃል።

ያጋሩ