ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የተቀመጡ ክለቦችን የሚያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታን የተመለከተ ዳሰሳ እንደሚከተለው አሰናድተናል።

በአንድ ነጥብ እና አንድ ደረጃ ብቻ ተበላልጠው የሊጉን ፉክክር በበላይነት እየመሩ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ነገ ምሽት 1 ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ የብዙዎችን ቀልብ በመያዝ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። በጨዋታው ባህር ዳር ከተማ ባገኘው የአሸናፊነት ጎዳና በመዝለቅ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው የሊጉን መሪነት ለመረከብ ሲጫወት ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ጥሩ ጎዳና የገባበትን ውጤት አስጠብቆ መሪነቱን ላለመልቀቅ የሚያደርገው ፍልሚያ ጠንካራ እንደሚሆን እሙን ነው።

የወቅቱ የሊጉ ምርጥ ቡድን የሆነው ባህር ዳር ከተማ ሽንፈት ካስተናገደ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ተቆጥረዋል። በሁለተኛው ሳምንት በጠባብ ውጤት በወልቂጤ ከተማ ከተረታ በኋላም ጨዋታ በጨዋታ ቅርፁን እያስተካከለ መጥቷል። በጣት የሚቆጠር ጊዜ ብቻ ቡድኑን የቅድመ ውድድር ዝግጅት ያሰሩት አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛውም በውድድር መሐል ቡድናቸውን እየሰሩ በመምጣት በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች ጠንካራ የሆነው ባህር ዳር ተፈጥሯል። ከምንም በላይ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ኮስታራ በመሆን ለተጋጣሚ ቡድን ምቾት የማይሰጥ አስፈሪ ሆኗል።

የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት በጥሩ ውጤት በመጀመር አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ቢያሸንፍም ከዛ ግን መጠነኛ የውጤት መንገራገጭ ገጥሞት ነበር። ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግን በተመሳሳይ በሦስት ጎሎች ብልጫ በማሸነፍ ወደ ቀድሞ አቋሙ ተመልሷል። በተለይ በሚታወቁበት የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጥቃት የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው በመንቀሳቀስ ቀጣዮቹን ደቂቃዎች የተጋጣሚን የራስ መተማመን አውርደው በተሻለ ነፃነት ለመጫወት የሄዱበት ርቀት ዋጋ አስገኝቶላቸው ነበር።

በሊጉ ጥቂት ግቦችን ያስተናገዱት የጣና ሞገዶቹ የኋላ መስመራቸው በአንፃራዊነት የተረጋጋ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። እርግጥ በሀዲያው ጨዋታ በመጠኑ ይህ የኋላ ውቅር ፈተናዎች በዝተውበት የነበረ ቢሆንም በግብ ብረቶቹ መካከል ቆሞ የነበረው ፋሲል የአጋሮቹን ክፍተት እያረመ ቡድኑ ለአራተኛ ጊዜ ግቡን ሳያስደፍር የወጣበትን ዕለት እንዲያሳልፍ አድርጓል። ከኳስ ጋር በቅይጥ አጨዋወት (ቀጥተኛ እና ኳስን ማንሸራሸር) ሲጫወት የሚታየው ባህር ዳር በተለይ የተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የሚፈጀውን ጊዜ በማሳጠር የአጥቂዎቹን ፍጥነት በማገናዘብ የግብ ምንጭ ለመፈለግ ይታትራል። ነገም በዚሁ መንገድ በዋናነት የመስመር አጥቂዎቹን ያማከለ አጨዋወት በመተግበር የቅዱስ ጊዮርጊስን የግብ ክልል ለመጎብኘት እንደሚጥር ይገመታል።

በአሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ፈረሰኞቹ ድል ባገኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች ወደ ራሳቸው የሜዳ ክልል ወረድ ብለው የሚጫወቱ ቡድኖችን ገጥመው ስድስት ግብ እና ስድስት ነጥብ ያገኙበት መንገድ በማጥቃቱ ረገድ አሁንም አስፈሪ እንደሆኑ ያሳያል። ጊዮርጊስ እንደ ቡድን የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን በተጫዋችም በሊጉ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ላይ ቀዳሚ አስመራጭ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በሊጉ ከኢትዮጵያ መድን በመቀጠል ከተለያዩ ተጫዋቾች ግብ ያለው ክለብ ስለሆነ የግብ አማራጮቹን ገምቶ ለመከላከል ያዳግታል። በእንቅስቃሴ ረገድም አዘውትሮ ቀጥተኛ አጨዋወትን ሲተገብር ቢታይም ያለፉትን ጨዋታዎች ጥሩ እየሆነ የመጣው የአማካይ መስመሩ መሐል ሜዳው ከመቆጣጠር ባለፈ ወደ ሳጥን ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን መፍጠሪያ አማራጭ እየሆነ ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎ ነገም በማይገመት አጨዋወት እንደሚንቀሳቀስ ሲጠበቅ ባህር ዳርም ለመከላከል ሊቸገር እንደሚችል ቀድሞ መናገር ይቻላል።

በሊጉ እስካሁን አንድ አንድ ጊዜ ብቻ የተሸነፉት ሁለቱ ቡድኖች ካሏቸው የተጫዋች ጥራት አንፃር ከቡድናዊ አጨዋወት ውጪ በግለሰብ ብቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ነገ ሊያሳዩ እንደሚችሉ ይገመታል። በየዲፓርትመንቱም ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት ሲጠበቅ ስህተትን ቀንሶ የሚገኘው ቡድን ለድል ቅርብ እንደሚሆን ይታሰባል። በዋናነት ግን ባህር ዳር ከተማ ጥቂት ግቦች ቢቆጠሩበትም በራሱ ሳጥን የሚሰራቸው ስህተቶች ዋጋ እያስከፈሉት ስለሚገኝ በራሱ ሳጥን ስል መሆን ይገባዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታዎችን የሚከውንበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ሲገባው በሁለቱ ጨዋታዎች የገጠማቸው ቡድኖች ኳስን መቆጣጠር የማይፈልጉ ስለነበሩና የነገው ተጋጣሚ ከእነርሱ በተቃራኒ ስለሆነ የተለየ ስልት መቀየስ ይገባዋል።

ባህር ዳር ከተማ በነገው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች እንደሌለ ታውቋል። በሀዲያው ጨዋታ ፊቱ ላይ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው የቡድኑ አምበል ያሬድ ባየም በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ግን ዳዊት ተፈራ፣ ሻሂዱ ሙስጠፋ እና ተመስገን ዮሐንስ ነገም ግልጋሎት የማይሰጡ ተጫዋቾች ናቸው።

ይህንን ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ሲመራው ፋሲካ የኋላሸት እና አብዱ ይጥና በረዳትነት በላይ ታደሰ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እንዲያገለግሉ ተመድበዋል፡፡

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– የሁለቱ ቡድኖች የእስካሁን ግንኙነት መከባበር ላይ የተመሰረተ ይመስላል። ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ስድስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለት ሁለት ጊዜ ተሸናንፈው በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ ስድስት ባህር ዳር ከተማ አራት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ፋሲል ገብረሚካኤል

ሳለዓምላክ ተገኘ – ፈቱዲን ጀማል – ያሬድ ባየ – ሔኖክ ኢሳይያስ

አለልኝ አዘነ – ቻርለስ ሪባኑ

ፉፁም ጥላሁን – ፉዐድ ፈረጃ – ዱሬሳ ጁቢሳ

ሀብታሙ ታደሠ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – አማኑኤል ተረፉ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ረመዳን የሱፍ

ሀይደር ሸረፋ – ጋቶች ፓኖም – ቢኒያም በላይ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – እስማኤል ኦሮ-አጎሮ – ቸርነት ጉግሳ