የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ መሪነቱን ሲረከብ ይርጋጨፌ ቡና እና ቦሌ ድል ቀንቷቸዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ሀዋሳ ከተማ ወደ መሪነት የመጣበትን ድል ሲቀዳጅ ይርጋጨፌ ቡና እና ቦሌ ክፍለከተማም ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል፡፡

የዕለቱ ቀዳሚ የነበረው የሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ 4 ሰዓት ሲል ተጀምሯል፡፡ በ3ኛው ሳምንት ከልደታ ጋር ነጥብ በመጋራታቸው ከመሪነት ፈቀቅ ብለው የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ መሪነት ለመመለስ ጠንካራ ትግልን አድርገው በመጨረሻም ድል ቀንቷቸዋል፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የበላይ መሆን የቻሉት ሀዋሳዎች ከወትሮው በተለየ የመሀል ክፍሉ ላይ ኳስን በማደራጀት ለአጥቂ ክፍሉ በማሻገር ግብ ለማግኘት ዋነኛ የጥቃት መንገዳቸው አድርገው ሲንቀሳቀሱ ተመልክተናል፡፡ አማካዩዋ ሲሳይ ገብረዋህድ እና ህይወት ረጉ በሚፈጥሩት የቅብብል ስብጥር እና በቱሪስት ለማ አማካኝነት የማይቋረጥ ጥቃት ሲሰነዝሩ የታዩት ሀዋሳዎች 7ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል ወደ ውስጥ ቱሪስት አሻግራ በሻዱ ረጋሳ ባስቆጠረችው ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመጀመሪያው አጋማሽ ድክመታቸው በሚገባ ተሻሽለው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ኳስን በመቆጣጠር ቢጫወቱም ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀሙ ረገድ ግን ደካሞች ነበሩ፡፡ 72ኛው ደቂቃ ላይም የሀዋሳ ተከላካዮች ኳስ በእጅ በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት የቅዱስ ጊዮርጊሷ አምበል ሶፋኒት ተፈራ ብትመታውም ፍሬወይኒ ገብሩ መልሳባታለች፡፡ ይህችን የፍፁም ቅጣት ምት ከሳቱ በኋላ መቀዛቀዝ የታየባቸው ጊዮርጊሶች 82ኛው ደቂቃ ላይ ሳራ ነብሶ ሁለተኛ ጎል አክላባቸው ጨዋታው በሀዋሳ 2ለ0 አሸናፊነት ተገባዷል፡፡ ቡድኑም ከንግድ ባንክ በድጋሜ የሊጉን መሪነት ተረክቧል፡፡

የጨዋታ ሳምንቱ አምስተኛ መርሃግብር በሆነው የይርጋጨፌ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ከቀትር በኋላ 8 ሰዓት ሲል ተከናውኗል፡፡ ተመሳሳይ የጨዋታ ይዘትን በተላበሰው እና ለዕይታ ብዙም ማራኪ ያልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ረጃጅም ብሎም ያልተሳኩ ቅብብሎች ያስመለከተን ነበር፡፡ አንፃራዊ ጥቃቶችን በመሰንዘሩ በሙሉ የጨዋታ ደቂቃው ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻለ አቀራረብ ቢኖራቸውም ከዕረፍት መልስ ተከላካዮቻቸው በሰሩት ስህተት 82ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው መስታወት አመሎ ግብ አስቆጥራ ይርጋጨፌ ቡና 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል፡፡

የጨዋታ ሳምንቱን የሚያሳርገው የዕለቱ የመጨረሻ መርሐ-ግብር በሁለቱ የአዲስ አበባ ክለቦች በሆኑት ቦሌ ክፍለ ከተማ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መካከል ተካሂዶ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር በቦሌ የበላይነት ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው አጀማመሩ የተመጣጠነ ቢመስልም በሒደት በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ አጥቂ ክፍሉ ኳሶችን ቶሎ ቶሎ በመጣል የበላይነት እየያዙ የመጡት ቦሌዎች 29ኛው ደቂቃ ላይ የንፋስ ስልክ ተከላካዮች ከጨዋታው ውጪ ነው ብለው በቆሙበት ቅፅበት አጥቂዋ ንግስት በቀለ በብልጠት ወደ ሳጥን እየገፋች ገብታ ኳስ እና መረብን አገናኝታ ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡ ኳስን አደራጅቶ መጫወትም ሆነ ለራሳቸውም የግብ ክልል ሽፋን በመስጠቱ ረገድ ደካማ የሆኑት እና በተቃራኒው በቦሌ የተበለጡት ንፋስ ስልኮች በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድ 34ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየው ሒርኮ ተጨማሪ ግብ አስቆጥራባቸዋለች፡፡

የአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻው ቡድን ቦሌ ከዕረፍት በኋላም የጨዋታ ብልጫውን ወደ ራሱ በመውሰድ ተጨማሪ ጎሎችን አክሏል፡፡ 64ኛ ደቂቃ ላይ ከንግስት በቀለ ጋር ተቀባብላ በመጨረሻም ለራሷ የደረሳትን ኳስ ስንታየው ሒርኮ ከቀኝ የንፋስ ስልክ የግብ አካባቢ ማራኪ ጎልን አድርጋው ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛ ኳስን ከመረብ አዋህዳለች፡፡ መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ሊጠናቀቅ መገባደጃው ገደማ አማካዩዋ ሜላት አልሙዝ ከሳጥን ውጪ አክርራ በመምታት ማራኪ የማሳረጊያ ጎል በማስቆጠር ጨዋታው ቦሌን 4ለ0 አሸናፊ አድርጎ ተፈፅሟል፡፡