የጨዋታ መረጃዎች | አዳማ ከተማ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

11ኛው የጨዋታ ሳምንት የሚጀምርበትን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አንስተናል።

ነገ የሚጀምረው 11ኛው የሊጉ የጨዋታ ሳምንት በወራጅ ቀጠናው ያሉት ሁለት ቡድኖች ይፋለሙበታል። ሰባት ነጥቦች ያሉት አዳማ ከተማ እና አምስት ነጥቦችን ከሰበሰበው ለገጣፎ ለገዳዲ እስካሁን ዕኩል ዘጠኝ ጨዋታዎች አድርገው በተመሳሳይ ስድስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግደዋል።

አዳማ ከተማ ከተከታታይ አራት ሽንፈቶች በኋላ ለዚህ ጨዋታ ደርሷል። ቡድኑ በአጠቃላይ ከገጠሙት ስድስት ሽንፈቶቹ ውስጥ በአራቱ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ግቦችን እያስተናገደ ይገኛል። በቅድሚያ ተቆጥሮበት ቀሪ ደቂቃዎችን ከተጋጣሚው ጋር ለመስተካከል የሚሄድበት መንገድም ለአዳማ ተፈላጊውን ውጤት ይዞ ሲመጣ አይታይም። ከዚህ ጋር በተያያዘ የቡድኑ የኋላ ክፍል ላይ በጉዳት እና በአቋም ተደጋጋሚ ለውጦች መደረጋቸውን ሲቀጥሉ አሁንም የስብስቡ ቀዳሚ የኋላ ደጀኖች አለመለየታቸው ለቀጣይ ጉዞውም ስጋት የሚሆን ነው። አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እና ረዳቶቻቸው ከተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቻቸው ምርጫ ባለፈ ፊት ላይም ከዳዋ ሆቴሳ በቀር በመስመር አጥቂ ሚና ላይም በቋሚነት ዕምነት የሚጥሉባቸው ተሰላፊዎችን ማግኘትም ይጠበቅባቸዋል። አዳማ ወረቀት ላይ ከሰሞኑ ተጋጣሚዎቹ አንፃር ውጤት ሊያገኝ የሚችልበት ጨዋታ እንደማድረጉ የተሻለ የማጥቃት ባህሪ ተላብሶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።

አዲስ አዳጊው ለገጣፎ ለገዳዲ ከነገ ተጋጣሚው የተሻለ በጎ ጎን የሚሆንለት ከስድስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርቶ ለነገው ጨዋታ መድረሱ ነው። ምንም እንኳን በጭማሪ ደቂቃ ነጥብ ለመጋራት ይገደዱ እንጂ ከቡና ጋር የተፋለሙበት መንገድ ለነገው ጨዋታ የሚተርፍ ነበር። ከኳስ ውጪ ክፍተቶችን በመዝጋት ከኳስ ጋር ለፊት መስመር ተሰላፊዎቹ በሚመች አኳኋን ያጠቃ የነበረበት መንገድ በሊጉ ጅማሬ ያሳየውን ጠንካራ አቋም መሳይ ነበር። የለገጣፎ አሰልጣኝ ቡድን አባላትም እነዚህን በጎ ጎኖች በነገው ጨዋታ ማስቀጠል እና ሙሉ ነጥብ ማሳካት ዋና የቤት ሥራቸው ይመስላል። ለገጣፎ ነገም የተጋጣሚውን የጨዋታ ፍሰት በመታተር ማቋረጥ እና ከቡናው ጨዋታ በተሻለ ድፍረት ቀጥተኛ ጥቃቶችን ለመሰንዘር እንደሚንቀሳቀስ ይጠበቃል።

በጨዋታው ጉዳት ላይ የሰነበተው የአዳማው ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ የተመለሰ ሲሆን የለገጣፎ ለገዳዲዎቹ ዮናስ በርታ እና አቤል አየለ አሁንም ጉዳት ላይ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ የሚገናኙበት ጨዋታ 10:00 ላይ ሲጀምር ፌደራል ዳኛ ሔኖክ አክሊሉ በመሀል ዳኝነት ፣ ፋንታሁን አድማሱ እና አንድነት ዳኛቸው በረዳትነት፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውበታል።