ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቋል

የ11ኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር የሆነው የአዳማ ከተማ እና ለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታ በአዳማ ድል አድራጊነት ተጠናቋል።

በ10ኛ የጨዋታ ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ አንድ ለምንም የተረታው አዳማ ከተማ ሦስት ነጥብ ካስረከበበት ጨዋታ ከግማሽ በላይ ተጫዋቾችን ለውጦ ወደ ሜዳ ገብቷል። በዚህም ደስታ ዮሐንስን በአብዲ ዋበላ ፣ ሚሊዮን ሰለሞንን በእዮብ ማቲያስ ፣ ፍሬድሪክ አንሳን በአድናን ረሻድ ፣ ዊሊያም ሰለሞንን በመስዑድ መሐመድ ፣ አቡበከር ወንድሙን በቦና ዓሊ እንዲሁም አብዲሳ ጀማልን በቢኒያም አይተን ቦታ ተክተዋል። በተመሳሳይ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ ሁለት አቻ የተለያየው ለገጣፎ ለገዳዲ በበኩሉ የአብቃል ፈረጃን ብቻ በብሩክ ብርሃኑ ለውጦ ጨዋታውን ቀርቧል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ቅፅበት የሆነው በአስራዎቹ ደቂቃ መባቻ ላይ የተፈፀመው ሁነት ነበር። ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ሲመራ የነበረው ሔኖክ አክሊሉ በተጫዋች ተጠልፎ በመውደቅ ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን በህክምና ባለሙያዎች እርዳታ ተደርጎለት እንዲቀጥል ቢሆንም ከሁለት ደቂቃዎች በላይ ማጫወት ሳይችል እያነባ ከሜዳ ወጥቷል። የእርሱን ኃላፊነትም አራተኛ ዳኛው ኃይለየሱስ ባዘዘው ተክቶ ሔኖክ እንዲረጋጋ ከተደረገ በኋላ በአራተኛ ዳኝነት ማገልገል ጀምሯል።

14ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተስተናግዶ ግብ ተቆጥሯል። በዚህም በአንፃራዊነት የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው ሲጫወቱ የነበሩት አዳማዎች አቡበከር ወንድሙ ከግራ መስመር የተሻማን ኳስ በግንባሩ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ሆነዋል። 

ከኳስ ውጪ ያለ አደረጃጀት ላይ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ መርጠው የነበሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ኢብሳን ዒላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች ቢልኩም በመጀመሪያው አጋማሽ ውጥናቸው እምብዛም አልሰመረም። አንድም ጊዜ የጠራ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

አዳማዎች ግብ ካገኙ በኋላ የማጥቃት ኃይላቸውን ገደብ አድርገው ቢጫወቱም 33ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን የሚያሳድጉበት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ከግራ መስመር የተሻማን ኳስ የጣፎው የግብ ዘብ ሚኪያስ ዶጂ በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ የተፋውን ኳስ አብዲሳ ጀማል አግኝቶት የነበረ ቢሆንም ዒላማውን ስቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በአዳማ አንድ ለምንም መሪነት ተጠናቋል።

መሪዎቹ አዳማዎች ሁለተኛውን አጋማሽ በፈጣን ጥቃት ነበር የጀመሩት። በዚህም ግብ አስቆጣሪው አቡበከር ከግራ መስመር አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ወጥቶበታል። ለገጣፎዎችም ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ሰጥተዋል። ከሳጥኑ ጨረቃ ትንሽ ራቅ ብሎ የተገኘውን የቅጣት ምት መሐመድ አበራ ቢመታውም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በ61ኛው ደቂቃ ደግሞ በአዳማ በኩል በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አቡበከር ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት በመጠቀም ጥሩ የቅጣት ምት መትቶ በተከላካዮች ተጨርፎበታል።

ጣፎዎች የማጥቂያ መንገዳቸውን ለማሻሻል አጥቂ እና የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን አስገብተው በተሻለ ወደ ላይኛው ሜዳ ለመድረስ ቢሞክሩም በ72 እና 73ኛው ደቂቃ በተቆጠሩባቸው ሁለት ግቦች እጅ ሰጥተዋል። በቅድሚያ ከግራ መስመር የተነሳን ኳስ ቦና ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሲመልሰው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አሜ መሐመድ ግብ አድርጎታል። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ይሄው ተጫዋች በፈጣን ሽግግር የተገኘን ኳስ በጥብቅ ምቱ መረብ ላይ አሳርፎታል። በጉዳት ከሜዳ የወጣውን ዳዋ ተክቶ የገባው አሜ በ85ኛው ደቂቃ ሐት-ሪክ የሚሰራበትን ዕድል ፈጥሮ መክኖበታል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።