የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 3-0 ለገጣፎ ለገዳዲ

👉”ለዚህ ድል ኃላፊነቱን የሚወስዱት ተጫዋቾቹ ናቸው” ይታገሱ እንዳለ

👉”አሁንም በትኩረት እና ልምድ ማጣት ዋጋ እየከፈልን ነው” ጥላሁን ተሾመ


አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው…

ጨዋታው ከዕረፍት በፊት የነበረው ነገር ተደጋጋሚ ሽንፈት ሲኖር ከዛ ለመውጣት ጥሩ አልነበረም። ከዕረፍት በኋላ ደግሞ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ተጫዋቾቹ ሲሻላቸው ሙሉ ቡድን ሲሆን የተሻለ ነገር ተከስቷል።

ስለ አሰላለፉ ለውጥ…

ዛሬ ይዘን የገባነው ለማሸነፍ ነው። ከዚህ በፊት ህመም ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ተሽሏቸዋል። ሜዳው እንደሚታየው ለመጫወት ብዙም አመቺ አይደለምና ያንን ታሳቢ በማድረግ ነው የበለጠ አጥቅቶ ለመጫወት ነው ተጫዋቾቹን ቀያይረን የገባነው

በሁለተኛው አጋማሽ ስላደረጉት ለውጥ…

ለዚህ ድል ኃላፊነቱን የሚወስዱት ተጫዋቾቹ ናቸው። ተደጋጋሚ ሽንፈት አንገት ያስደፋል። እረፍት ሰዓትም ውጤቱን እንደምንፈልገው ተነጋግረናል። ግን በመቸኮል እንደማይሆን አውርተን ወደ ሜዳ ገብተናል። የተጫዋች ቅያሪዎቹም ጥሩ ነበሩ። ከእረፍት በኋላም የተሻለ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ተጫውተን አሸንፈናል።

የዛሬው ሦስት ነጥብ…

ተከታታይ ሽንፈቶች ከባድ ናቸው። ከዚህ ለመውጣት አንድ ነጥብ ያስፈልገን ነበር። እግዚአብሔር ይመስገን።

አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ – ለገጣፎ ለገዳዲ

ስለጨዋታው….

በጨዋታው ተበልጠናል ፤ 3ለ0 በሆነ ውጤትም ተሸንፈናል። ይህ የሚያስከፋ ውጤት ነው።

ቡድኑ ላይ ሽንፈት ስለመበርከቱ…

ከዛሬው ጨዋታ በፊት ከቡና ጋር ነበር የተጫወትነው። በጨዋታው ጥሩ ነበርን። በዛ ሞራል እንመጣለን ብለን ነበር። ከቡነሰው ጨዋታም ከአንድ ተጫዋች በስተቀር ምንም ለውጥ አላደረግንም ነበር። ግን ያንን ማስጠበቅ አልቻልንም። አሁንም በትኩረት እና ልምድ ማጣት ዋጋ እየከፈልን ነው። እንዳልኩል የነበርንበትን ነገር ለማስጠበቅ ጉጉት ነበር። ካለንበት ደረጃም ለመውጣት ጉጉት አለ። በአጠቃላይ ዛሬ እንደቡናው ጨዋታ አይደለም የተጫወትነው። በጣም የወረደ አጨዋወት ነው የተጫወትነው።