በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የሚገኙትን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በርከት ባሉ የሁለቱ ቡድኖች ተጓዥ ደጋፊዎች ታጅቦ ተጀምሯል። ሁለቱም ተጋጣሚዎች የመጨረሻ ጨዋታዎቻቸውን ያሸነፉበትን የመጀመሪያ አሰላለፍ ሳይቀይሩ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።
ፍልሚያው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከሳጥን ሳጥን ምልልስን ቢያስመለክትም የጠሩ የግብ ሙከራዎች ግን አልበረከቱበትም። 10ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተሰንዝሯል። በዚህም ፉዐድ ፈረጃ ሳጥኑ መግቢያ ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ቢልከውም ባህሩ ነጋሽ መልሶበታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ የባህር ዳርን የግብ ክልል የደረሰው በ22ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህም ሱሌይማን ያሻማውን የቅጣት ምት ፍሪምፖንግ ለመጠቀም ጥሮ መክኖበታል።
በአንፃራዊነት ባህር ዳር በተሻለ ኳሱን በፍጥነት በመቀባበል ወደ ላይኛው ሜዳ ለመድረስ ሲሞክር ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማግኘት ተንቀሳቅሷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ካልታሰበ ምንጭ ፈረሰኞቹ ግብ ሊያገኙ ነበር። በዚህም ፍሪምፖንግ ሜንሱ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ሳጥን ውስጥ ያሻማውን ኳስ የባህር ዳር ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ሳይናበቡ ቀርተው መዳረሻው መረብ ሊሆን ነበር። በጭማሪው ደቂቃ ደግሞ በባህር ዳር በኩል ኳስ በእጅ በመንካቱ ምክንያት የተገኘን የቅጣት ምት ፍፁም ጥላሁን መትቶት ግብ ጠባቂ ባህሩ በሚገርም ቅልጥፍና አውጥቶታል። አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ወሳኝ ተጫዋቻቸው ጋቶች ፓኖምን በጉዳት የቀየሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የአማካይ መስመራቸው በመጠኑ የሳሳ ቢመስልም በጥሩ ቅብብል በ54ኛው ደቂቃ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥረው ተመልሰዋል። በዚህም አማኑኤል ገብረሚካኤል በቀኝ መስመር ተጫዋች እየቀነሰ በመግባት መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን የላከውን ጥሩ ኳስ ሀይደር እና ናትናኤል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
ደፈር በማለት የተከላካይ አማካይ በመቀነስ የማጥቃት ባህሪ ያለው ተጫዋች ወደ ሜዳ ያስገቡት የጣና ሞገዶቹ አሁንም ፈጣኖቹን የመስመር ተጫዋቾቻቸው ያማከለ የፊትዮሽ እንቅስቃሴ ማድረግ ቀጥለዋል። በ66ኛው ደቂቃም ዱሬሳ ሹቢሳ ከኦሴ ማውሊ በደረሰው ኳስ ጥብቅ ምት ወደ ግብ ልኮ ዒላማውን ስቶበታል። ከደቂቃ በኋላ ግን ፈረሰኞቹ ወዲያው ፈጣን ጥቃት አድርገዋል። በዚህም ቸርነት ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን መሪ ሊያደርግ ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። በቀሪ ደቂቃዎችም ጨዋታው ያን ያህል ግብ ጠባቂን የሚፈትን ሙከራ ሳያስተናግድ ቀርቷል። የሁለቱም ክለብ ተጓዥ ደጋፉዎችም በሚገርም ሞራል ቡድናቸውን ሲያበረታቱ አምሽተው ጨዋታው በሠላም ተጠናቋል።