የአሠልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 0-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

👉”ጨዋታው ውጤቱ ብዙ ትርጉም ይኖረው ነበር። አቻ ነው የተፈቀደልን ፤ ተቀብለናል” ደግአረገ ይግዛው


👉”አቻ መውጣቱን አንፈልግም ፤ ግን ጠንካራ ጨዋታ ስለሆነ ምንም ዓይነት ስሜት አልተሰማኝም” ዘሪሁን ሸንገታ

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው…
​​
ጨዋታው እንደታየው ጠንካራ ጨዋታ ነው። ጊዮርጊስም ልምድ ያለውና ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ያሉበት ቡድን ነው። የኛም ተጫዋቾች በ90 ደቂቃ ውስጥ ውጤት ይዞ ለመውጣት ያላቸውን ሁሉ በሜዳ ላይ ሰጥተዋል ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን ገድለን እንድንወጣ የሚያስችሉን አጋጣሚዎች ነበሩ። ከጉጉት በመነጨ የበለጠ ደግሞ ጨዋታውን የማሸነፍ ፍላጎታቸው ከፍ ያለ ስለነበር በቀላሉ መጠቀም የሚቻለውን ኳስ ወደ ቡድን ሥራ ማስገባት ሲገባ የግል አጠቃቀም ላይ ባደረጉት ጥረት አባክነናል። እንደ ጨዋታ ካየነው ግን በ90 ደቂቃ በነበረን ወደጎልም ከመቅረብ አኳያ ጫና ፈጥረን ከመጫወት አኳያ የተሻለ ተንቀሳቅሰናል ብዬ አስባለሁ። ጨዋታው ውጤቱ ብዙ ትርጉም ይኖረው ነበር። አቻ ነው የተፈቀደልን ፤ ተቀብለናል።

በጨዋታው የተፈጠሩ የግብ ዕድሎች ብዙ ስላለመሆናቸው…

ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ነው። እንደገለፅኩት የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ፍጹም ወደ ጎል መቀየር የሚችሉ ዕድሎችን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ አግኝተን ነበር። እንደተባለው በሁለታችንም በኩል ውጥረቱ ከፍ ያለ ነበር። የጨዋታውን ብልጫ እና ውጤቱን ወደ ራስ የመውሰድ ትግል ነበረው ፤ ጉሽሚያም የበዛበት ጨዋታ ነበር። የዕለቱ ዳኛም ፈቅደዋል ማለት ይቻላል። አጎሮን አይተህ ከሆነ ስድስት ጥፋቶችን ፈፅሟል ግን ምንም ካርድ ያላየበት ሁኔታ ነው ያለው። በዛሬው ጨዋታ ተከላካዮቻችን ከሚገባው በላይ ዋጋ ከፍለዋል። እንደ አጠቃላይ ግን መልካም የሚባል ውጤት ነው።

በሁለተኛው አጋማሽ ስላደረጉት የአደራደር ቅርፅ ለውጥ…

የእኛ ቡድን አጥቅቶ መጫወት ነው መታወቂያው። ቻርልስ በቆየበት ጥሩ ለማገዝ ሞክሯል ውጤቱን ወደኛ መውሰድ ግን ትልቅ ጥቅም ስለሚኖረው የተወሰኑ ደቂቃዎችን ሁለት የማጥቃት ባሕርይ ያላቸውን አማካዮች በመጠቀም የበለጠ ክፍት ቦታዎችን ለማግኘት ጥረት አድርገናል። ባሰብነው ልክ ተሳክቶልናል ብለን አናስብም ፤ ፍላጎታችን ጎል ከማግኘትም አኳያ የተሻለ ሥራ እንሠራለን ብለን ነበር ያሰብነው። ሆኖም እነሱም መከላከል ላይ ጠንክረው ነበር የሚጫወቱት። እንደሌላው ጊዜ እንደሚታወቀው የመስመር ተከላካዮች በማጥቃት ላይ የነበራቸው ተሳትፎ የተገደበ ነበር። ከእኛ የጨዋታ መንገድ ጋር በተያያዘ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል እና እኛም በምንፈልገው ልክ ክፍት ቦታዎችን ለማግኘት አልቻልንም። ያሰብነው ጎል ማግኘት ነበር አልተሳካልንም።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው…

በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ማጥቃት ቦታ እንሄዳለን ግን አመርቂ አልነበረም። ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የተሻለ ነው፡፡ ቶሎ ቶሎ ወደ ኳስ እንደርሳለን። አንዳንድ ኳሶቻችን ይቆራረጣሉ እንጂ ጨዋታው ካለው ውጥረት እና ሁለታችንም ጋር ካለው ጫና አንፃር መጥፎ አይደለም የተጫወትነው፡፡

በጨዋታው ላይ ስለነበረው ውጥረት…

ሁለታችንም በአንድ ዓይነት ሁኔታ ስህተት ላለመስራት ነበር የምንፈልገው፡፡ ስህተቶች እንዳይሰሩ ሁለታችንም ጋር ጥንቃቄ አለ። አንዳንድ ኳሶቻችንም ይቆራረጣሉ። እነርሱም ጋር እኛም ጋር ኳሶች የሚወድቁበት ቦታ ልክ አይደሉም። አቻ ሆነው መውጣት ስለፈለጉ መጨረሻ አካባቢ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ብዙ የመውደቅ ብዙ የሆነ ነገር የማድረግ ነበር፡፡ በአጠቃላይ እግር ኳሱ ሁለታችንም ጋር ጥሩ ነው፡፡

ስለ አቻ ውጤቱ ተገቢነት

ምንም ማድረግ አትችልም ካላሸነፍክ አቻም ሽንፈትም አለ፡፡ አቻ መውጣቱን አንፈልግም ግን ጠንካራ ጨዋታ ስለሆነ ምንም ዓይነት ስሜት አልተሰማኝም፡፡