ኢትዮጵያ ቡና ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር በይፋ ሊለያይ መቃረቡን ሶከር ኢትዮጵያ ከታማኝ ምንጮቿ አረጋግጣለች።
ከ2012 ጀምሮ እስካለፈው የውድድር ዓመት ድረስ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ሲመራ የቆየው ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር ውጤታማ አለመሆን ጋር ተያይዞ በይፋ በመለያየት በምትኩ በክረምቱ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ከ2015 ጀምሮ እስከ 2016 መጨረሻ ድረስ በሁለት ዓመት ውል ማስፈረሙ ይታወሳል፡፡ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ በማምጣት አሰልጣኙ ስራቸውን የጀመሩ ሲሆን ያለፉትን አስር የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችንም ቡናማዎቹን በኃላፊነት መርተዋል፡፡
ክለቡ ዘንድሮ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ክለቡ ለዋንጫ እፎካከራለሁ ብሎ ከአሰልጣኙ ጋር ውል የገባ ቢሆንም ቡድኑ በአራት ጨዋታዎች ሲሸነፍ በአራቱ ድል ቀንቶት በሁለት ጨዋታዎችም አቻ ለመለያየት ተገዷል፡፡
በ11ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በዛሬው ዕለት ሀድያ ሆሳዕናን ገጥሞ 1ለ0 ክለቡ ከተረታ በኋላ የክለቡ አመራሮች በተደጋጋሚ በሚታየው የውጤት መጥፋት የተነሳ ከአሰልጣኙ ጋር ሊለያይ ስለ መቃረቡ በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ከገባው ውል አንፃር እየተመዘገበ ያለው ውጤት ከተጠበቀው በታች መሆኑን ተከትሎ በነገው ዕለት የክለቡ አመራሮች አሰልጣኙን ካወያዩ በኋላ በይፋ እንደሚሰናበትም አውቀናል፡፡