ከፍተኛ ሊግ | የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

በቶማስ ቦጋለ እና በጫላ አቤ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ 12 ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ ነቀምት ከተማ ፣ ሻሸመኔ ከተማ ፣ ሀምበርቾ ዱራሜ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ችለዋል።

የ03፡00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ በምድብ ‘ሀ’ 03፡00 ላይ የሰበታ ከተማ እና የባቱ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር የታየበት ሲሆን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ባቱዎች የተሻሉ ነበሩ። 37ኛው ደቂቃ ላይ የሰበታው አምበል ዮሐንስ አድማሴ ኢዩኤል ሳሙኤል ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት አሸብር ውሮ ሲመታ ግብ ጠባቂው መቆጣጠር ባለመቻሉ የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ተስፋዬ በቀለ በቀላሉ አስቆጥሮ አሳዎቹ የመጀመሪያውን አጋማሽ መሪ ሆነው እንዲወጡ አስችሏል።

ባቱዎች ከዕረፍት መልስ በፈጣን ሽግግሮች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲጀምሩ 47ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ ደረጀ በግራ መስመር በጥሩ ሁኔታ ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ለተስፋዬ በቀለ ሲያቀብል ተስፋዬ ያደረገውን ሙከራ የሰበታው ግብጠባቂ ሚሊዮን ሰለሞን በግሩም ቅልጥፍና አድኖበታል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላም ተደጋጋሚ ጥቃት ያስተናገዱት ሰበታዎች ይባስ ብሎም 58ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ታደሠ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ራሱ ላይ አስቆጥሮት ጨዋታቸውን ይበልጥ አክብደዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ባቱዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ሲጫወቱ 77ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ግርማ በጥሩ አጨራረስ ሰበታን ለባዶ ከመሸነፍ ያዳነች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በባቱ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ ነቀምቴን የተከታታይ ድል ባለቤት አድርጎ በጨረሰው የምድብ ‘ለ’ ጨዋታ ቦዲቲ ከተማዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ በዮርዳኖስ እያሱ ጎል ቀዳሚ መሆን ችለው ነበር። ሆኖም ነቀምቴዎች 20ኛው ደቂቃ ላይ በአምሳሉ መንገሻ አቻ መሆን ሲችሉ ዳንኤል ዳዊት ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ እንዲሁም ተመስገን 30ኛው ደቂቃ ላይ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ግቦች 3-1 መምራት ችለዋል። ቦዲቲዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ዳንኤል ከመረብ ካገናኛት ሁለተኛ ግብ በላይ መራመድ ባለመቻላቸው ጨዋታው በነቀምት 3-2 አሸናፊነት ተደምድሟል።

ሆሳዕና ላይ በምድብ ‘ሐ’ የተደረገው የኮልፌ ክ/ከተማ እና የጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ የመጀመሪያውን አጋማሽ ጅማ አባ ጅፋር የተሻሉ ጫናዎችን በተደጋጋሚ ለመፍጠር ሲጥሩ የታዩ ቢሆንም ጨዋታው ግብ ሳያስመለክተን ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል። በሱራፌል እና በአሚር የሚመራው የጅማ አባ ጅፋር አማካይ ስፍራ ግልፅ የሆነ የበላይነት ተስተውሏል። ሆኖም በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ጅማ አባ ጅፋሮች የተሻለ ወደፊት ተጠግተው መጫወት ቢችሉም ኮልፌ ክ/ከተማ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ሲፈጥሩ ታይቷል። ይሄ ውጥናቸው ሰምሮም በ88ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት በፈጠሩት ጫና ያገኙትን የማዕዘን ምት በጨዋታው ከግብ ጠባቂው ሀብታሙ ከይሬ ጋር የተሳካ ጊዜን ያሳለፈው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ቢንያም ትንሳኤ በግንባር አስቆጥሮ ጣፋጭ 3 ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

የ 05፡00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ በምድብ ‘ሀ’ የጋሞ ጨንቻ እና የሰንዳፋ በኬ ጨዋታ ሲደረግ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ጋሞ ጨንቻዎች የተሻሉ ነበሩ። የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራም 40ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ለገሠ ዳዊት ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካደላ ቦታ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት በድንቅ ሁኔታ ሞክሮት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሰኮንዶች ሲቀሩ አምበሉ ፋሲል ደስታ ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ያዳነበት ኳስ በሰንዳፋ በኬዎች በኩል የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጋሞዎች ማጥቃታቸውን ሲቀጥሉ አጨራረስ ላይ የነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ ግን ከኳስ ፍሰታቸው ጋር ያልተመጣጠነ ነበር። ለአብነት ያህል 62ኛው ደቂቃ ላይ በፈቃዱ ሕዝቅኤል አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ከግብጠባቂው ጋር 1 ለ 1 የተገናኘው ገረሱ ገላዬ ኃይል ባልነበረው ሙከራ የግብ ዕድሉን ሲያባክን ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ሰለሞን ጌታቸው አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው በፈቃዱ ሕዝቅኤል ግብ ጠባቂውን አታልሎ በማለፍ ኳሱን ለቡድን አጋሮቹ ከማቀበል አማራጮች ጋር ለማስቆጠር ምቹ ቦታን ቢያገኝም በደካማ አጨራረስ ትልቅ የግብ ዕድሉን አባክኗል። 82ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ጌታቸው ከረጅም ርቀት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን ጋሞ ጨንቻ 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በዚሁ ሰዓት ጅማ ላይ በተደረገ የምድብ ‘ለ’ ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ 20ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ተሾመ ያስቆጠረውን ጎል አስጠብቆ በመጨረስ ቂርቆስ ክፍለከተማን 1-0 አሸንፏል።

ሆሳዕና ላይ በምድብ ‘ሐ’ የካ ክ/ከተማን ከዳሞት ከተማ ሲያገናኝ ጨዋታው የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበትና አነስተኛ የግብ ሙከራ የታየበት ሲሆን በሁለቱም ክለቦች በኩል ጠንካራ የተከላካይ መስመር አስመልክቷል። በዳሞት በኩል የመሀል ተከላካዮቹ አብዱ በድሩ እና ወርቁ አዲስ በየካ ክ/ከተማ በኩል የኋላ መስመር ተጫዋቾቹ ጋቱ ጎዴሞ እና ዲም ኬር የተሳካ ጊዜ ማሳለፍ ሲችሉ ሁለቱም ክለቦች ግባቸውን ሳያስደፍሩ ጨዋታው ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል።

የ08፡00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ በምድብ ‘ሀ’ የቤንች ማጂ ቡና እና የጅማ አባ ቡና ጨዋታ ሲደረግ በኳስ ቁጥጥሩ ብርቱ ፉክክር የታየበት ቢሆንም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን በሁለቱም በኩል ደካማ እንቅስቃሴ አሳይቶናል። ጅማ አባ ቡናዎች የመጀመሪያውን የተሻለ የግብ ዕድል 33ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ዘላለም አበበ ከግራ መስመር ለ ጃፈር ከበደ አመቻችቶ ቢያቀብልም ጃፈር በደካማ አጨራረስ የግብ ዕድሉን አባክኗል። ከዕረፍት መልስ 47ኛው ደቂቃ ላይ ቤንች ማጂ ቡናዎች ፈጣን የማጥቃት ሲያደርጉ እሱባለው ሙሉጌታ ከቀኝ መስመር ወደግብ ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ሳንመለከትበት ያለግብ ተጠናቋል።

ጅማ ላይ በተካሄደው የምድብ ‘ለ’ ጨዋታ ደግሞ አምቦ ከተማ ጫላ ከበደ በመጀመሪያው ብሩክ ቸርነት ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀንን 2-0 መምራት ችሎ ነበር። ሆኖም ፕሪምየር ሊጉ ላይ አምና በመቻል ከዛ ቀደም ደግሞ በድሬዳዋ እና ወልዋሎ የሚታወቀው ገናናው ረጋሳ እንዲሁም በአዳማ ፣ ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ የተጫወተው ኃይሌ እሸቱ ያስቆጠሯቸው ግቦች ጨዋታው 2-2 ተጠናቆ ሰሜን ሸዋ ነጥብ እንዲጋራ አድርገዋል።

ሆሳዕና ላይ በምድብ ‘ሐ’ በዛ ያለ ደጋፊ የተገኘበት የስልጤ ወራቤ እና የሶዶ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ በመጀመሪያው አጋማሽ ፈጣን እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴ የታየበት እና በዛ ያሉ የግብ ሙከራዎችን ያስመለከተን ቢሆንም ግብ ሳይቆጠርበት አጋማሹ ተጠናቋል። ከዕረፍት መልስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ጨዋታው በአመዛኙ በስልጤ ወራቤ ቁጥጥር ውስጥ ያለ ቢመስልም ሶዶዎች የተገኙትን አጋጣሚዎች ለመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በስልጤ ወራቤ በኩል የተገኙትን የግብ ሙከራዎች የሶዶ ከተማው ግብ ጠባቂ አቡሽ አበበ ድንቅ በሆነ ሁኔታ እያመከነ በጨዋታው የተሳካ ጊዜን አሳልፏል ፤ ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

የ10፡00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ በምድብ ‘ሀ’ አዲስ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ያደረጉት ጨዋታ ሁለት ዓይነት መልኮች የነበሩት ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ አቃቂዎች በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ ከተማዎች የበላይነቱን ወስደዋል። 22ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ በኃይሉ ወገኔ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ አቃቂን መሪ ማድረግ ሲችል ከግቧ በኋላ የጠራ የግብ ዕድል ሳያስመለክተን አጋማሹ ተጠናቋል። ከዕረፍት መልስ አዲስ ከተማዎች ተሻሽለው ሲቀርቡ 53ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዓለማየሁ ከረጅም ርቀት የመታውና ግብ ጠባቂው ወደ ውጪ ያስወጣው ኳስ በጨዋታው የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራቸው ነበር። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት አዲስ ከተማዎች 76ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ይሄውም ሄኖክ ካሉ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው አሸናፊ በቀለ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በጨዋታው የተሳካ ጊዜን ያሳለፈው የአቃቂው ግብ ጠባቂ ጁቤድ ኦመድ ግብ ከመሆን አግዶታል። አቃቂዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ በመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ታግዘው ጨዋታውን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ጅማ ላይ የተደረገው የዕለቱ አራተኛ ጨዋታም እንደ ሦስተኛው ጨዋታ ሁሉ ከኋላ ተነስቶ ነጥብ መጋራትን ያስመለከተን ነበር። እንጅባራ ከተማ በአበበ ታደሰ እና ባህሩ ፈጠነ ግቦች ጨዋታውን ቢያጋምስም ጉለሌ ክፍለከተማዎች ከዕረፍት መልስ ጁንዴክስ አወቀ እና ልዑል ገ/እግዚአብሔር ባስቆጠሯቸው ግቦች ነጥብ መጋራት ችለዋል።

ሆሳዕና ላይ በምድብ ‘ሐ’ ሀምበሪቾን እና ሮቤ ከተማን ሲያገናኝ ጨዋታው ፍጥነት የበዛበትና በአብዛኛው ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ በግብ ሙከራ የታጀበ እና በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ ለማግባት ጥረት የተስተዋለበት ቢሆንም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል። ጨዋታው ከዕረፍት መልስም በተመሳሳይ በብርቱ ፉክክር የታጀበ ለተመልካች አዝናኝ ሆኖ ሲቀጥል በአንጻራዊነት ሀንበሪቾዎች የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል። በ50ኛው ደቂቃ የሀምበሪቾው የፊት መስመር ተጫዋች ዳግም በቀለ ከመስመር በኩል የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ሀምበሪቾን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሀምበሪቾ ከተማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ሰዓት አልቆ የባከኑ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በፍቃዱ አስረሳኝ በማስቆጠር ጨዋታው በሀምበሪቾ 2-0 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል። የሀምበሪቾ ዱራሜን የኋላ መስመር በመምራትና ቡድኑን በአንበልነት እየመራ የነበረው እንዳለ ዮሐንስ እና አጥቂውን ከኋላ በመሆን ሲያግዝ የነበረው ቃለአብ በጋሻው ከተመልካቾች ዘንድ አድናቆት ተችሯቸዋል።