ሪፖርት | መድን ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

ኢትዮጵያ መድን ጨዋታው ሊገባደድ ደቂቃዎች ሲቀሩት ያሬድ ዳርዛ ባስቆጠራት ግብ ወልቂጤ ከተማን ረቷል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ወልቂጤ ከተማዎች የግብ ዘባቸው ፋሪስ አላዊን ብቻ በጀማል ጣሰው ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከሀዋሳ ጋር በተመሳሳይ ነጥብ ተጋርተው የመጡት ኢትዮጵያ መድኖችም የመስመር አጥቂያቸው ብሩክ ሙሉጌታን ብቻ በሀቢብ ከማል ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታም እንደ መጀመሪያው መርሐ-ግብር የመጀመሪያ ሙከራውን ያስተናገደው በ6ኛ ደቂቃ ነበር። አብዱልከሪም መሐመድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ኪቲካ ጅማ በመቀስ ምት ሞክሮት ለጥቂት ዒላማውን ስቶበታል። የሚያገኟቸውን ኳሶች በፈጣን ሽግግር ወደ ኢትዮጵያ መድን ግብ ክልል ለመውሰድ ሲጥሩ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በ27ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑሪን የፈተነ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። በዚህም የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበድ ራቅ ካለ ቦታ ያገኘውን የቅጣት ምት መሬት ለመሬት መትቶት አቡበከር እንደ ምንም መልሶታል።

ከኳስ ጋር ጊዜ በማሳለፍ የተሻሉት መድኖች በተለይ ወደ ቀኝ መስመር አድልተው ሠራተኞቹን ለመቅደም ሲጥሩ የነበረ ሲሆን በ31ኛው ደቂቃም በዛው ቀኝ መስመር የተሻገረን ኳስ ኪቲካ ሳይጠቀምበት በቀረው ዕድል ጥቃት ሰንዝረዋል። መድን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመሩው ደቂቃ የቅጣት ምት አግኝቶ አጋጣሚውን ሀቢብ ከማል በድንቅ ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎት መሪ ሆኖ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ታትረው መጫወት ይዘዋል። በ56 እና 58ኛው ደቂቃም ጥሩ ዕድል ፈጥረው አቻ ሊሆኑ ተቃርበው ነበር። በቅድሚያ አቡበከር ሳኒ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ያገኘውን ኳስ ዒላማውን አስቶ ወደላይ ሲመታው በመቀጠል ደግሞ ፋሲል አበባየሁን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አፈወርቅ ኃይሉ በመጀመሪያ ንክኪው በግንባሩ ሞክሮ ተመልሶበታል።

በእጃቸው የገባውን ውጤት ማስጠበቅን እያሰቡ ወልቂጤ ለማጥቃት ሲወጣ ከጀርባ የሚገኘውን ቦታ በማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማግባት የወጠኑ የሚመስሉት መሪዎቹ መድኖች ከቆመ ኳስም ቢሆን በ67ኛው ደቂቃ ቡጢ ሰንዝረው ነበር። በዚህም የግቡ ባለቤት ሀቢብ ያሻማውን የቅጣት ምት አብዱልከሪም መሐመድ ግብ ሊያረገው ጥሮ አግዳሚውን ታኮ ወጥቶበታል።

ጨዋታው 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ወልቂጤዎች የልፋታቸውን ውጤት አግኝተዋል። በዚህም አብዱልከሪም መሐመድ አቡበከር ሳኒ ላይ ጥፋት ሰርቶ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ጌታነህ ከበደ ወደ ግብነት ቀይሮት አቻ ሆነዋል። ከመምራት ወደ አቻነት የተሸጋገሩት መድኖች ዳግም መሪ ለመሆን በ83ኛው ደቂቃ ኪቲካ በሞከረው ጥብቅ ኳስ ሞክረው ለጥቂት ወጥቶባቸዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ሲሞን ፒተርን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ያሬድ ዳርዛ ከግራ መስመር የተሻማን ኳስ በግንባሩ አስቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን አሸናፊነት ተጠናቋል። በጭማሪው ደቂቃ ግን ወልቂጤ ሁለት ጥሩ ዕድሎችን ከቆመ ኳስ እና ከክፍት ጨዋታ ፈጥሮ ወጥቶበታል።