የአሠልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-1 ሀዲያ ሆሳዕና

👉”ጨዋታው ከመሪዎቹ እንዳንርቅ ይረዳን ስለነበረ ጠንካራ ፉክክር ነው ያደረግነው” ያሬድ ገመቹ


👉”ዛሬ ደስ ያለኝ ነገር እንቅስቃሴያችን ማደጉ ነው። እንቅስቃሴ ማደግ ከቻለ ነገ የማታሸንፍበት ምንም ምክንያት የለም” ተመስገን ዳና

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለጨዋታው….

ጠንካራ ፉክክር ነበር። እኛ ከሽንፈት ነው የመጣነው ፤ እነርሱ ደግሞ ነጥብ ተጋርተው ነው የመጡት። ጨዋታው ከመሪዎቹ እንዳንርቅ ይረዳን ስለነበረ ጠንካራ ፉክክር ነው ያደረግነው።

ቀድመው ግብ አስቆጥረው ውጤቱን ለማስጠበቅ ስላደረጉት እንቅስቃሴ…

የመከላከል ቅርፃችንን ይዘን በእነርሱ በኩል የምናገኛቸውን ስህተቶች ለመጠቀም ነበር ያሰብነው። ይሄም ተሳክቶልናል። ቀድመንም ግብ ጠባቂያቸው ተሳስቶ ግብ አግኝተን ያንን ግብ አስጠብቀን ወጣን።

ቡድኑ ላይ ስላለው የተጫዋች ጉዳት…

ብዙ ተጫዋቾች ተጎድተውብናል። ድሬዳዋ ባለ አንድ በሽታም ተጫዋች ታሞብን አጠቃላይ 7 እና 8 ተጫዋቾች ተጎድተውብን አብረውን የሉም። ይህንን ተከትሎ ወጣቶችን ቀላቅለን ነው እየተጫወትን ያለነው።

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው…

ዛሬ የሀዲያ አጨዋወት ሽግግር ላይ መሰረት ያደረገ ነበር። ከማጥቃት ወደ መከላከል እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረጉ ሽግግሮች ላይ ፈጣን ነበሩ። ስለዚህ ተረጋግተን ኳሱን ተቆጣጥረን መጫወት እንዳለብን ነበር ያወራነው። ዛሬ የግብ ዕድሎችን ከመጨረስ ውጪ ከሞላ ጎደል ቡድናችን ጥሩ ነው። ጥሩ ቡድን ነው ያየሁት ዛሬ።

በጨዋታው ውጤት ማግኘት ስላልቻሉበት ምክንያት…

የተከላካይ እና አጥቂ መስመሩ ላይ የነበረው ውህደት በጣም አሪፍ ነው። ነገር ግን ፊት መስመር ላይ የነበረን ግንኙነት የተሳሳተ ነበር። በእንቅስቃሴም በአብዛኛው እየጠፋን ነበር ስንመለስ የነበረው ፤ በተለይ ፊት መስመር ላይ። ስለዚህ እነዚህ ችግሮች የጎል ዕድሎችን እንዳንጨርስ አድርጎናል። እንደ አጠቃላይ ግን ጥሩ ቡድን ነበር የነበረን።

ቡድኑ ላይ ስለሚታዩ የተጫዋቾች እና የአደራደር ለውጦች…

እንደየጨዋታዎቹ የተጫዋቾችን ፎርሜሽን ልትቀይር ትችላለህ። ዛሬ የመረጥነው አጨዋወት ምንም እንኳን በውጤት ባይታጀብም በእንቅስቃሴ ጥሩ አድርጎናል። ስለዚህ ቋሚ ፎርሜሽን የለንም። እንደየጨዋታው ልንለዋውጥ እንችላለን። ዛሬ ባየነው ነገር ግን ደስተኛ ነኝ።

ከውጤት ጋር በተገናኘ…

ዛሬ ደስ ያለኝ ነገር እንቅስቃሴያችን ማደጉ ነው። እንቅስቃሴ ማደግ ከቻለ ነገ የማታሸንፍበት ምንም ምክንያት የለም። አሁን ያን ያህል የሚያስጨንቅ ነገር አለ ብዬ አላስብም።