አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን በውጤት መጥፋት የተነሳ ሊለያይ የቻለው ኢትዮጵያ ቡና በጊዜያዊ አሰልጣኝ እንደሚመራ ታውቋል፡፡
ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ትላንት ከቀትር በኋላ በ11ኛው ሳምንት ጨዋታውን አድርጎ አራተኛ ሽንፈትን ለማስተናገድ የተገደደው ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በውላቸው መሠረት ውጤት እያስመዘገቡ አይደለም በማለት ሊለያይ ከጫፍ መድረሱን ምሽት ላይ ገልፀን የነበረ ሲሆን አሠልጣኙም በዛሬው ዕለት ከክለቡ አመራሮች ጋር ለመነጋገር እንደሚጓዙ አሳውቀናችሁ ነበር፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን በደረሳት መረጃ መሠረት ደግሞ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ወደ አዲስ አበባ ከደቂቃዎች በፊት በነበረው በረራ ያቀኑ ሲሆን ከክለቡ አመራሮች ጋር በተለያዮ ጉዳዮች በስምምነት ለመለያየት ከተወያየ በኋላ ከክለቡ ጋር በይፋ ይለያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። በቀጣይም ኢትዮጵያ ቡና በጊዜያዊነት በቀድሞው የክለቡ ተጫዋች እና የአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ረዳት ሆኖ ሲሰራ የነበረው ዮሴፍ ተስፋዬ እና አምና የካሣዬ አራጌ ረዳት በመሆን የሰራው ገብረኪዳን ነጋሽ (ጋምብሬ) በጣምራ እንደሚመራ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአሰልጣኝ ቡድን አባል የሆነው ነፃነት ክብሬም አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ ከክለቡ ጋር እንደሚቀጥል ይጠበቃል።