ሪፖርት | ብርትካናማዎቹ ዐፄዎቹን ከመመራት ተነስተው አሸንፈዋል

በመቀመጫ ከተማቸው አልቀመስ ያሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ፋሲል ከነማን ረተዋል።

ከቀናት በፊት የ2ኛ ሳምንት ተስተካካት መርሐ-ግብሩን ከወላይታ ድቻ ጋር አድርጎ አንድ ለምንም የተረታው ፋሲል ከነማ ሦስት ነጥብ ካስረከበበት ፍልሚያ አራት ተጫዋቾችን ለውጧል። በለውጦቹም መናፍ ዐወል ፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ወንድማገኝ ማርቆስ አርፈው አስቻለው ታመ ነ፣ አምሳሉ ጥላሁን ፣ ታፈሰ ሠለሞን እና ጉልላት ተሾመ ወደ ሜዳ እንዲገቡ ተደርጓል። በ10ኛ ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ሁለት አቻ የተለያዩት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ አብዩ ካሣይ ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ብሩክ ቃልቦሬን በዳንኤል ተሾመ ፣ አብዱለጢፍ መሐመድ እና ዮሴፍ ዮሐንስ ምትል በአሰላለፋቸው ቦታ ሰጥተዋል።

የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ ገና በ4ኛው ደቂቃ መሪ አግኝቷል። በአንፃራዊነት የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች ከመልስ ውርወራ የተገኘን ኳስ ዓለምብርሃን ይግዛው ከሽመክት ጉግሳ ተቀብሎ ሲያሻማው ፍቃዱ ዓለሙ ገጭቶት መሪ ሆነዋል። ድሬዳዎች ግን ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን አጋጣሚ መፍጠር የጀመሩት ወዲያው ነበር። በዚህም በ10ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ያሻማውን የመዓዘን ምት ግዙፉ ተከላካይ አሳንቴ ጎድፍሬድ በግንባሩ መትቶት ቡድኑን አቻ ለማድረግ ቢጥርም ግብ ጠባቂው ሜኬል ሳማኬ በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም የፋሲል ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ የመጨረሻ ኳስ የደረሰው ቢኒያም ጌታቸው የግብ ዘቡን መውጣት ተከትሎ የመታው ተንጠልጣይ ምት ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል። በተመሳሳይ ሁኔታም ይሁ ተጫዋች ቢኒያም በ17ኛው ደቂቃ ሌላ ሙከራ ሰንዝሮ መክኖበታል።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ጫናዎች የበዛባቸው ፋሲል ከነማዎች በተደጋጋሚ የኋላ መስመራቸው በሚፈጥራቸው ስህተቶች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማስተናገድ ይዘዋል። በ29ኛው ደቂቃ ኤልያስ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ጥሩ ብቃት እያሳየ የነበረው ሳማኬ ሲመልሰው ከሰከንዶች በኋላ የተሻማው የመዓዘን ምት ግን መዳረሻው መረብ ሆኗል። በዚህም አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ያሻማውን የመዓዘን ምት በቅርቡ ቋሚ የነበረው ቢኒያም ጌታቸው በግንባሩ ግብ አድርጎታል።

እጅግ ተነቃቅተው ጨዋታውን እየከወኑ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች አቻ ከሆኑ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ራሱ ቢኒያም አሳንቴ ጎድፍሬድ ከራሱ ክልል ያሻማውን የቅጣት ምት ሳጥኑ መግቢያ ላይ ሆኖ በመቀበል በጥሩ አጨራረስ ቡድኑን ወደ መሪነት ያሸጋገረ ጎል አድርጎታል። ፋሲሎች በ4ኛው ደቂቃ ግብ ካገኙ በኋላ ግብ ጠባቂ የፈተነ ጥቃት ለማድረግ 41 ደቂቃዎችን ጠብቀው የቅጣት ምትን መነሻ ባደረገ ኳስ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ቢያደርጉም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል። አጋማሹም በድሬዳዋ ከተማ መሪነት ተጠናቋል።

ብርትካናማዎቹ የሁለተኛውን አጋማሽም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በጥሩ ሁኔታ መከወን ይዘዋል። ገና በ48ኛው ደቂቃም ኤልያስ አህመድ ከቻርለስ ሙሴጌ ተቀብሎ በሞከረውና ግብ ጠባቂው ሳማኬ በመለሰው አጋጣሚ መሪነታቸው ለማስፋት ሞክረዋል። በአጋማሹ አማካይ በመቀነስ አጥቂ ወደ ሜዳ ያስገቡት ፋሲሎች በበኩላቸው በ57ኛው ደቂቃ ቅያሪያቸው ፍሬ ሊያፈራ ነበር። በዚህም ታፈሰን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሀብታሙ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ተገኝቶ በጠበበው አንግል የመታው ኳስ በግብ ዘቡ አብዮት ካሣይ ተመልሷል።

በአንፃራዊነት በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ፋሲል ከነማዎች በተደጋጋሚ በተጋጣሚ ሜዳ ለመድረስ ቢታትሩም ጠጣሩን የድሬዳዋ የኋላ መስመር ማስከፈት አልቻሉም። ከፋሲል ተጫዋቾች እንደ ሳማኬ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሽመክት በ78ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ለገባው ሱራፌል ዳኛቸው ጥሩ ኳስ ሰጥቶት ሱራፌል ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ ምናልባት ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረበች አጋጣሚ ነበረች። ድሬዳዋዎች በበኩላቸው ጥቃት መሰንዘራቸውን ገታ አድርገው መከላከል ላይ ተጠምደዋል። በ87ኛው ደቂቃ ግን ፍቃዱ ግቡን ባስቆጠረበት መንገድ በግንባሩ ጥሩ ዕድል ፈጥሮ የግቡ አግዳሚ ባይመልስበት አቻ ሊሆኑ ነበር። በቀሪ ደቂቃዎች ፋሲል በሙሉ ኃይሉ ቢያንስ የአቻ ውጤት ለማግኘት ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ጨዋታውም በድሬዳዋ 2ለ1 አሸናፊነት ተገባዷል።