በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በሦስት መርሐግብሮች ሲጀመር አርባምንጭ ከተማ ከግማሽ ደርዘን በላይ ጎል አስቆጥሮ ሲያሸንፍ መሪዎቹ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ድል ቀንቷቸዋል፡፡
ዘጠኝ ጎሎችን ያስመለከተን የአርባምንጭ ከተማ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ፍፁማዊ የአርባምንጭ ከተማ ብልጫ እና ከደርዘን በላይ ጎሎችን አስመልክቶን በእንስት አዞዎቹ ድል አድራጊነት ተጠናቋል፡፡ ከመጀመሪያው አጋማሽ ጀምሮ የማጥቃት የኃይል ሚዛናቸውን ወደ ራሳቸው አድርገው በተጋጣሚያቸው ላይ ጫናን በጊዜ ማሳደር የጀመሩት አርባምንጮች 9ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል አጥቂዋ ቤተልሄም ታምሩ ቆንጆ ጎል አስቆጥራ ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡ ምንም የማጥቃት ፍላጎትን ያጡት ንፋስ ስልኮች ፋታ የለሽ ጥቃትን ለማስተናገድ በመገደዳቸው ቤተልሄም ታምሩ የግል አቅሟን ተጠቅማ ሁለት ጎሎችን አከታትላ በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርታለች፡፡ 31ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩዋ ትውፊት ካዲኖ ከሳጥን ውጪ ማራኪ አራተኛ ጎልን ከመረብ አዋህዳ በአርባምንጭ 4-0 መሪነት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል፡፡
ከዕረፍት መልስ የአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልዱ አርባምንጭ ከተማ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወቱም ሆነ ተደጋጋሚ የግብ ዕድልን በመፍጠሩ ረገድ አሁንም የተዋጣላቸው ሆነው ዘልቀዋል፡፡ 53ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሄም ታምሩ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት ወደ ጎል የላከቻት ኳስ የግብ ጠባቂዋ ሚሪንዳ ጨመረ ግልፅ ስህተት ታክሎበት ኳሷ መረብ ላይ አርፋለች፡፡ ቤተልሄምም ለራሷ አራተኛ ለቡድኗ አምስተኛ ግብ አድርጋለች፡፡ ጫናዎች የተበራከቱባቸው እና የአርባምንጭን ጥቃት መቋቋም ሲሳናቸው የታዩት ንፋስ ስልክ ላፍቶዎች በአርባምንጯ ተከላካይ ድርሻዬ መንዛ ስህተት አንድ ጎል አስቆጥረው የነበረ ቢሆን ቤተልሄም ታምሩ ሁለት ጎሎችን አከታትላ አስቆጥራ ስድስት ጎሎችን በአንድ ጨዋታ ማስቆጠር ችላለች፡፡ ተቀይራ የገባችው ድንቅነሽ በቀለ 85ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አክላ ጨዋታው በአርባምንጭ 8-1 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ለአርባምንጭ ግማሽ ደርዘን ጎሎችን ያስቆጠረችው ቤተልሄም ታምሩ የጨዋታው ምርጥ በመባል ተሸልማለች፡፡
የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ከቀትር በኋላ 8 ሰዓት ሲል በሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል የተደረገ ነበር፡፡ ጠንካራ የመሸናነፍ ፉክክር ባስተዋልንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከጅምሩ ጀምሮ ፋታ የለሽ ተደጋጋሚ የማጥቃት ጥረት ማየት የቻልንበት ነበር፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች ከመሀል ክፍሉ ከሚነሱ ኳሶች መሀል ለመሀል ለአጥቂዎቹ በማሳለፍ ለመጫወት የጣሩ ሲሆን በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ከመስመር አልያም ከኋላ ተመስርቶ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ገብቶ ጎሎችን ለማግኘት ብርቱ ጥረት በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉበት ቢሆንም ኳስ እና መረብ ተገናኝተው ልንመለከት አልቻልንም፡፡
ጨዋታው ከዕረፍት ተመልሶ ሲቀጥል ገና አጋማሹ በተጀመረ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ሀዋሳ ከተማ መሪ መሆን ችሏል፡፡ ከቀኝ የድሬዳዋ የግብ አቅጣጫ የመስመር ተከላካዩዋ በሻዱ ረጋሳ ወደ ጎል ስትልከው ኳሱ ቋሚውን ብረት ነክቶ ሲመለስ ኳሷን ለማውጣት በተፈጠረ ግርግር ረዳት ዳኛዋ ይልፋሸዋ አየለ መስመር አልፏል በሚል ግቡን አፅድቀዋለች፡፡ የድሬዳዋ ከተማ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ግቧ አልገባችም በሚል በተፈጠረው ውዝግብ ጨዋታው ለሁለት ደቂቃዎች ተቋርጦ ቀጥሏል፡፡ ጨዋታው 52ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም ከሳጥን ውጪ የሀዋሳዋ አጥቂ ረድኤት አስረሳኸኝ ወደ ጎል አክርራ ስትመታ የግቡ ቋሚ መትቶ ሲመለስው ከግቡ ትይዩ ቆማ የነበረችው ግብ ጠባቂዋ ሳራ ብርሀኑን ኳሷ ገጭቷት ወደ ጎልነት ተለውጧል፡፡ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ድሬዳዋዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በታደለች አብርሃም አማካኝነት ጎል ቢያገኙም ቱሪስት ለማ የዓመቱ አምስተኛ ግቧን በማከል በሀዋሳ 3-1 ድል ጨዋታው ተፈፅሟል፡፡ የሀዋሳ ከተማ የመሀል ተከላካይ ቅድስት ዘለቀ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጨዋታው ምርጥ በመባል ተሸልማለች።
የማሳረጊያ ጨዋታ የሆነው እና ጠንካራዎቹን ሁለት ክለቦች ያገናኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ንግድ ባንክ በመጀመሪያው አጋማሽ የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅመው ባስቆጠሩት ሁለት ጎሎች ድል ተጎናፅፈዋል፡፡ 4ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ወደ ግራ የሜዳው ክፍል ብርቱካን ገብረክርስቶስ ያሻገረችውን ኳስ በተከላካዮች የአሸፋፈን ስህተት የተነሳ አረጋሽ ካልሳ ብልጠቷን ተጠቅማ የደረሳትን ኳስ ወደ ጎል ለውጣው ንግድ ባንክን ቀዳማ አድርጋለች፡፡ ኤሌክትሪኮች የሚሰሩትን ስህተት ለመጠቀም ወደ ኋላ ሳይሉ የዘለቁት ንግድ ባንኮች 26ኛ ደቂቃ ላይ አምበሏ ሎዛ አበራ ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የቀጠለው ጨዋታው ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ተመጣጣኝ ፉክክርን ያስመለከተን ቢሆንም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ከመመልከት አንፃር እምብዛም ነበር፡፡ ከፉክክር አንፃር ቀዝቀዝ ባለው በዚህኛው አጋማሽ ከተመለከትናቸው ሁነቶች ዋነኛው በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የንግድ ባንኳ ተከላካይ ሀሳቤ ሙሶ እና የኤሌክትሪኳ አጥቂ ትንቢት ሳሙኤል በፈጠሩት አለመግባባት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግደዋል፡፡ ጨዋታው 2-0 በንግድ ባንክ አሸናፊነት የተገባደደ ሲሆን የቡድኑ አማካይ ሰናይት ቦጋለ በበኩሏ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተመርጣለች፡፡