የአሠልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-2 ድሬዳዋ ከተማ

👉”ሜዳችን ላይ ውጤታማ የሆንበት ትልቁ  ምክንያት አንድ መሆናችን ነው ፤ እንደ ቡድን ቀለማችን አንድ ነው” ዮርዳኖስ ዓባይ

👉”በጭንቀት ማድረግ የምትፈልገውን ነገር ማድረግ ይሳንሀል ፤ ስለዚህ ያንን ነገር ነው እያየን ያለነው” ኃይሉ ነጋሽ

ዮርዳኖስ ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ከዚህ በፊት እንደሚገባብን ዛሬም ግብ ተቆጥሮብናል። ያንን ነገር ማስተካከል አልቻልንም ግን ምንም ማድረግ አትችልም። ቀጣይ ያንን ነገር ለማስተካከል የመጀመሪያ 10 እና 15 ደቂቃ መጠንቀቅ አለብን ተባብለን ነው ሁሌም የምንገባው ግን ያጋጥማል። ይሄንን ቶሎ ለመለወጥ የምናደርገው ነገር ወሳኝነት አለው። ከዕረፍት በፊት ሁሉንም ነገር እንጨርሳለን ከዕረፍት በኋላም ግን ጭንቀት አለ። ይሄን ውጤት ለማስጠበቅ መረጋጋት ነበረብን። የተሻሉ ነገሮች አግኝተን ነበር ፤ ግን ይበልጥ እየመራህም እየተመራህም መረጋጋት ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ይመስገን ውጤቱን ይዘን ወጥተናል።

ከዕረፍት መልስ ያደረጉት እንቅስቃሴ ውጤት ለማስጠበቅ ስለመሆኑ…

በጣም የሚገርመው ነገር እንኳን ውጤቱን ለማስጠበቅ አይደለም ሰዓት መግደል የሚባል ነገር የለም ተባብለን ነው የገባነው። ምክንያቱም በ45 ደቂቃ ብዙ ነገር ይሠራል ፤ በ45 ደቂቃ ነው ሁለት ለአንድ ያሸነፍነው። ስለዚህ አምስት እና አስር ደቂቃ ሲቀር ሰዓት ልትገድል ትችላለህ። አሁንም እያጠቃን ሌላ ጎል መፈለግ አለብን ተባብለን ነው የገባነው ግን እዛ ያሉት ተጫዋቾች መረጋጋታቸው ያለውን ጨዋታ የማንበብ አቅማቸው የእነሱ ነው። ሁለተኛውን አጋማሽ በጣም በጭንቀት ውስጥ ነው የተጫወትነው ፤ ሦስት ነጥቡ ትልቅ ነው ለእኛ።

ሜዳቸው ላይ ውጤታማ የመሆናቸው ምስጢር…

ሜዳችን ላይ ውጤታማ የሆንበት ትልቁ  ምክንያት አንድ መሆናችን ነው። እንደ ቡድን ቀለማችን አንድ ነው። ለምሳሌ ብርቱካናማ ነው የእኛ ቀለም ከዛ ውጪ ቀለም የለንም። ስለዚህ በዲስፕሊንም ልምምድ ላይም በሁሉም ነገር አንድ ነን። ውስጥ ምንም እንከን የለም። ከተጫዋቾቹ ጋር ያለን መግባባት ፣ እርስበርስ ያላቸው መግባባት ፤ ውስጥ  እንደ ድንጋይ የጠነከረ አንድነት አለ ያ ነው ውጤታማ ያደረገን ብዬ ነው የማስበው።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ስለተፈጠረው ግርግር…

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በተፈጠረው ግርግር የእግርኳስ ቤተሰቡን ይቅርታ መጠየቅ እንፈልጋለን።

ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታውን ለማሸነፍ ነበር የመጣነው ፤ ተጫዋቾቻችን ላይ ትንሽ ጫና የነበረው ጨዋታ ነበር። ይህም ከውጤት ማጣት የተነሳ እንጂ ሌላ ችግር አልነበረውም፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በሰራናቸው ስህተቶች ዋጋ ከፍለናል። በተለይ የቆሙ ኳሶች ጠብቀን ነበር። እዛ ላይ በሰራናቸው ስህተቶች ጎል ተቆጥረውብናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ተሸንፈን ወጥተናል፡፡

ስለተሸነፉበት ምክንያት…

የራሳችን ድክመት ነው፡፡ አንድ ካገባን በኋላ ወደ ኋላ ሸሽተን ነበር። ይሔም የሚያሳየው ተጫዋቾች የፍርሀት ሳይሆን ውጤትን በመፈለግ በጭንቀት መጫወታቸውን ነው። እኔ የማምነው ኳስን ይዘህ በመጫወት ነው ግን ያንን ስላላደረጉ ወደ ኋላ በመሸሻችን ሁለት ጎል ተቆጠረብን። ከዕረፍት በኋላ ማድረግ የሚገባንን አድርገናል ብዬ አስባለሁ ግን ዞሮ ዞሮ ውጤት አጥተናል፡፡

ስለጫና…

እኔ ምንም ጫና የለብኝም ፤ ተጫዋቾች ላይ ግን ያው ፋሲል ሁሌም አሸናፊ ነው፡፡ በጭንቀት ማድረግ የምትፈልገውን ነገር ማድረግ ይሳንሀል ፤ ስለዚህ ያንን ነገር ነው እያየን ያለነው፡፡