የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በ11ኛው የጨዋታ ሳምንት በታዩ የዲስፕሊን ግድፈቶች ላይ በመመስረት የቅጣት ውሳኔዎች ሲያስተላልፍ ድሬዳዋ ከተማ የሳምንቱ ከፍተኛው ቅጣት ተጥሎበታል።
11ኛው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ሳምንት ሰባት ፍልሚያዎችን አስተናግዶ ትናንት ተፈፅሟል። ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ሥነስርዓት ኮሚቴ ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርቶች ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በግለሰቦች ደረጃ በተላለፉ ቅጣቶች በሀዋሳ ከተማ እና መቻል ጨዋታ የቀይ ካርድ የተመለከተው ተባረክ ሄፋሞ የሦስት ሺህ ብር እና የሦስት ጨዋታዎች ቅጣት ሲጣልበት የወልቂጤ ከተማ የቡድን መሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ታዳሙ ከኢትዮጵያ መድን ጋር በነበረው የቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ወቅት ከ15 ደቂቃ በላይ ዘግይተው በመምጣታቸው 1000 ብር ተቀጥተዋል።
በክለቦች ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕና በሳምንቱ ጨዋታ የቡድኑ አምስት ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ 5000 ብር ሲቀጣ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከፍተኛውን ቅጣት አስተናግዷል። በዚህም ክለቡ ከፋሲል ከነማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ደጋፊዎቹ አፀያፊ ስደብ በመሳደባቸውና ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው የብር ሰባ አምስት ሺህ እንዲሁም በተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ላይ ቁሳቁስ በመወርወራቸው የብር ሃያ አምስት ሺህ በድምሩ የብር አንድ መቶ ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎበታል።