ለገጣፎ ለገዳዲ በአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ላይ ውሳኔ አሳልፏል

በውጤት ማጣት መነሻነት አሰልጣኞቹን የጠራው የለገጣፎ ለገዳዲ ቦርድ የስንብት እና የማስጠንቀቂያ ውሳኔዎችን ሰጥቷል።

በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተሰተፈ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ የመጀመርያ ጨዋታውን ሀዋሳ ከተማን በመርታት በድል በመጀመር ብዙዎችን አስደንቆ ነበር። ሆኖም እንደ አጀማመሩ ያላማረለት ቡድኑ በሁለት ጨዋታ ነጥብ ከተጋራ በኋላ በሰባት ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዶ በደረጃው ሠንጠረዡ ግርጌ ለመቀመጥ ተገዷል።

በዚህ ሒደት ደስተኛ ያልሆኑ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ቡድኑ ከአዳማ ከተማ በተረታበት ጨዋታ በአካል ተገኝተው ከተከታተሉ በኋላ በውጤቱ ደስተኛ ባለመሆን እና በቀጣይ ክለቡ በሚስተካከልበት ጉዳይ ለመምከር የቡድኑ የአሰልጣኝ አባላት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ ትናንት ውይይት አድርገው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።

በዚህም መሠረት ረዳት አሰልጣኝ የሆኑትን ዳዊት ይፍሩ ፣ እዮብ ዋቢ እና ድሪባ ጃንቦ ሦስቱንም ማሰናበታቸው ሲታወቅ ውጤት የማሻሻል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ፍቃዱ ገብሩ ለቀጣይ ጨዋታ ቡድኑን እያዘጋጁ ወደ ድሬዳዋ ተመልሰዋል።