መረጃዎች | 43ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ 12ኛ ሳምንት የሚጀምርባቸውን ሁለት የነገ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን አሰናድተናል።

መቻል ከ ወልቂጤ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ ከድል እና ከሽንፈት የተመለሱት መቻል እና ወልቂጤን ያገናኛል። መቻል ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ሀዋሳን በመርታት ከድል ጋር ተገናኝቶ ነጥቡን 12 ማድረስ ችሏል። ከነገ ተጋጣሚያቸው በአራት ደረጃዎች ከፍ ብለው 6ኛ ላይ የተቀመጡት ወልቂጤዎች ደግሞ የዓመቱን አራተኛ ሽንፈታቸውን በኢትዮጵያ መድን እጅ አስተናግደዋል።

ከደካማ አጀማመሩ እፎይ የሚልበትን ውጤት ያሳካው መቻል በሀዋሳው ጨዋታ ከውጤት ባሻገር በእንቅስቃሴ ረገድ ያሳየውን ጠንካራ ጎን ማስቀጠል ዋነኛው የነገ ዓላማው ይመስላል። በሀዋሳው ጨዋታ በበመከላከሉም በማጥቃቱም የተሻለ እንቅስቃሴ በማሳየቱ ከድል ጋር ከመታረቁ ጋር ተደምሮ ነገ የተሻለ የሥነልቦና ደረጃ ላይ ሆኖ ጨዋታውን የሚጀምር መቻል ይጠበቃል። ባተለይም ፍፁም ዓለሙ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ያሳዩት እንቅስቃሴ ለቡድኑ የነገ የማጥቃት ዕቅድ መሰረት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።

ሠራተኞቹ ከለገጣፎው ድል በኋላ በሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ቢያሳኩም የሰበሰቡት ነጥብ እና ያሉበት ደረጃ የሚያስከፋ አይደለም። ሆኖም በነዚህ ጨዋታዎች ቡድኑ ያስቆጠራቸው ሦስት ጎሎች ከጌታነህ ከበደ ብቻ መገኘታቸው ቡድኑ የፊት መስመሩ ላይ አማራጮችን ማስፋት በተለይም ከእነየኋላሸት ሰለሞን ቀደም ሲል የነበረውን ብቃት ማግኘት ይጠበቅበታል። ከማጥቃት አማራጮች ባለፈ የወልቂጤ ከተማ የሁለተኛ አጋማሽ በተለይም የመጨረሻ ደቂቃዎች ትኩረት ማጣት አሁንም ያልተቀረፈው እና ለነገውም ፍልሚያ መታረም ያለበት ድክመቱ ነው። ለአብነት ያህል በቅርብ ጨዋታዎች ቡድኑ ያለፈው ሳምንት የመድኑን ሽንፈት ጨምሮ ከድሬዳዋ እና ከጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ሲጋራ ከ87ኛው ደቂቃ በኋላ ሦስት ግቦችን አስተናግዷል።

በነገው ጨዋታ መቻል ተሾመ በላቸውን ብቻ በጉዳት የሚያጣ ሲሆን በወልቂጤ ከተማ በኩል ፋሪስ አለዊ ፣ ቴዎድሮስ ሀሙ እና ውሀብ አዳምስ በጉዳት ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።

ይህንን የ10:00 ጨዋታ ኤፍሬም ደበሌ በመሀል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ እና ለመጀመሪያ ጊዜ ረዳት ዳኛ በመሆን የተመደበው ኤልያስ መኮንን በረዳትነት ፣ በተመሳሳይ ከከፍተኛ ሊጉ በቅርቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ባሪሶ ባላንጎ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል፡፡

ሀዲያ ሆሳዕና ከ አዳማ ከተማ

የምሽቱ ጨዋታ ከቆይታ በኋላ ወደ ድል የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኛል። ሀድያ ሆሳዕና ከሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ካሳካበት ውጤት ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት አገግሞ በ18 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አዳማ ከተማ በበኩሉ ለገጣፎ ለገዳዲን በመርታት የዓመቱን ሦስተኛ ድሉን በማስመዝገብ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ተቀምጧል።

ነብሮቹ ወደ ድል በተመለሱበት የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ቀላል የማይባሉ ጠንካራ ጎኖችን አሳይተዋል። ቡድኑ ምንም እንኳን በርካታ ጉዳቶች ቢኖሩበትም ተጋጣሚን ያማከለ የጨዋታ ዕቅድ ይዞ በመግባት ያሸነፈበት መንገድ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው። በተለይም ከኳስ ውጪ የነበረው አደረጃጀት በቀላሉ ክፍተት የማይሰጥ ሆኖ የታየ ሲሆን ከዚህ በፊት ቡድኑ ላይ ይታይ የነበረው ፈጣን ሽግግር የማድረግ ጥንካሬው ተመልሶ ታስተውሏል። የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ እነዚህን ነጥቦች አስቀጥለው ይበልጥ በፉክክሩ ይዘልቃሉ ወይ የሚለውን ለማየት የነገው ጨዋታ ወሳኝ ይሆናል።

በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ በጊዜ ግቦችን እያስተናገደ በቀሪ ደቂቃዎች ብዙ ጉልበት ያወጣ የነበረው አዳማ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲን ሲረታ በተቃራኒው በቶሎ ግብ በማስቆጠር ጨዋታውን በራሱ መንገድ ማስኬዱ ነገሮችን ቀለል አድርጎለታል። ይህንን ጠንከር ካለ ተጋጣሚ ጋር ለመድገም ደግሞ የነገው ጨዋታ ማሳያ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል። አዳማ የሚሊዮን ሰለሞንን መመለስ ተከትሎም በኋላ መስመሩ ላይ የተሻለ መረጋጋት ማሳየቱ እንዲሁም ፊት ላይም አቡበከር ሳኒ እና አሜ መሐመድ ያሳዩት መልካም እንቅስቃሴ ነገም ተመሳሳይ አቋም እንዲያሳዩ የሚያስጠብቅ ነው።

ምሽት 01:00 ላይ በሚጀምረው ጨዋታ ከሀዲያ ሆሳዕና ባዬ ገዛኸኝ በቅጣት ቤዛ መድህን እና እንዳለ ደባልቄ በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን መለሰ ሚሻሞ እና ራምኬል ሎክ ከጉዳት ተመልሰዋል፡፡ በአዳማ ከተማ በኩል አሁንም ከጉዳቱ ያላገገመው ዳዋ ሆቴሳ ከነገውም ጨዋታ ውጪ ሲሆን በመጨረሻው ጨዋታ መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው መስዑድ መሐመድ ግን ለነገው ጨዋታ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ተጋጣሚዎቹ እስካሁን በሊጉ ስድስት ጨዋታዎችን ሲያደርጉ ሀዲያ ሆሳዕና ሁለት እንዲሁም አዳማ ከተማ ሦስት ዕድሎችን አሳክተዋል። በጨዋታዎቹ አዳማ ከተማ ሰባት ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ስድስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

መቻል እና ወልቂጤ ዓምና በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ በመጀመሪያው ዙር መቻል 2-1 አሸንፎ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ያለ ግብ ተለያይተዋል።

በጨዋታው ዳንኤል ግርማይ በመሀል ዳኝነት ፣ አማን ሞላ እና ፍቅሬ ወጋየሁ በረዳትነት ፣ ባህሩ ተካ በአራተኛ ዳኝነት የተመደቡ ዳኞች ናቸው፡፡