ድሬደዋ ከተማ የተወሰነበት ውሳኔ እንዲነሳለት ጠየቀ

ድሬደዋ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ተከትሎ አወዳዳሪው አካል በክለቡ ላይ የወሰነው የዲሲፒሊን ውሳኔ እንዲነሳለት በደብዳቤ ጠይቋል።

በ11ኛው ሳምንት ካገናኘው ጨዋታ መካከል ድሬዳዋ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር ባከናወኑት ጨዋታ የድሬደዋ ደጋፊዎች አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸውና የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ላይ ቁሳቁስ ስለመወርወራቸው ሪፖርት በመቅረቡ ክለቡ በድምሩ ብር 100000 /አንድ መቶ ሺህ/ እንዲከፍል አወዳዳሪው አካል ቅጣት ማሳለፉ ይታወሳል።

ክለቡ ቅጣቱ እንዲነሳለት በፃፈው ደብዳቤ በ10ኛው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ጌታነህ ከበደ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ባልተገባ መልኩ ደስታውን በመግለፅ ደጋፊውን እንዳነሳሳ እና ለዚህም ተጫዋቹ ይቅርታ የጠየቀ ቢሆንም ድሬዳዋ ሀምሳ ሺህ ብር መቀጣቱን አስታውሷል። ቀጥሎም በፋሲሉ ጨዋታ ደግሞ ሽመክት ጉግሳ ያሳየውን ደካማ አቋም ለመሸፈን ያልተገባ ምልክት በማሳየት ደጋፊዎችን ወደ አላስፈላጊ ስሜት እንዲገቡ አድርጓል ብሏል። በዚህም አጥፊዎቹ ሳይቀጡ ክለቡ ‘በአንድ ጥፋት ሁለት እጅግ የተጋነነ ቅጣት ሊጣልብኝ አይገባም’ የሚል አቋሙን አንፀባርቋል።

ድሬዳዋ ከተማ በደብዳቤው እንዳለው ችግሮቹ የክለቡን ደጋፊዎች የማይወክሉ እና የሚወገዙ መሆናቸውን ፣ እንዳይደገሙ እንደሚሰራም በመግለፅ እና የድሬደዋ ደጋፊ በጨዋታ ከተበለጠ ለተቃራኒ ቡድን የሚደግፍ ሚዛናዊ ደጋፊ መሆኑ የሚታወቅ መሆኑን በማንሳት ቅጣቱ እንዲነሳለት ጠይቋል።